ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን እና አሜሪካ ከስምምነቱ ምን አተረፉ? ስምምነቱስ ጸንቶ ይቀጥላል?
ኢራን እና አሜሪካ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ መሆናቸውን እየገለጹ ነው። ነገር ግን ከዚህ በኋላም አስቸጋሪ የድርድር ሁኔታዎች ይጠብቋቸዋል።
ለኢራን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ የተኩስ አቁም ያህል ዋጋ አለው። ኢራን በጦርነቱ ጠንክራ መውጣቷን ማሳያ አድርጋም ወስዳዋለች።
ቴህራን፤ አሜሪካ እና እስራኤልን በመደበኛ ጦርነት ማሸነፍ ግቧ አልነረበም። እስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ሳይፈርስ ወደ ድርድር ጠረጴዛው መሄድ ተጠቃሚ ያደርጋታል። የመግባቢያ ሰነዱ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው።
ስምምነቱ በ60 ቀናት ውስጥ ስለ ኢራን ኒውክሌር ውይይት ማድረግን ያካትታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ስምምነቱ ላይ በተናጠል ፊርማቸውን አኑረዋል።
ስምምነቱ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ውጊያ ማቆምን፣ ሉዓላዊነትን ማክበርን፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈትን እንዲሁም አሜሪካ በኢራን የባሕር መተላለፊያ ላይ የጣለችው ክልከላ መነሳትን ያካትታል።
ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች እንዲተላለፉ ለማገዝ ተስማምታለች።
በስምምነቱ መሠረት የኒውክሌር መሣሪያ ለመገንባት የሚውል የበለጸገ ዩራኒየም ማከማቸት አትችልም።
አሜሪካ የኢራን የነዳጅ ባለሙያዎች ላይ የተጣለ ክልከላ ማንሳትን ጨምሮ ማዕቀብ የተጣለባቸው የቴህራን ሃብቶች ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ ማመቻቸትም ይጠበቅባታል።
ከማዕቀቦችን ከማላላት በተጨማሪ ለመልሶ ግንባታ የሚውል ቢያንስ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚመደብም ተጠቁሟል።
የመግባቢያ ሰነዱን የኢራን ባለሥልጣናት እንደ ድል አድርገው የሚያቀርቡበት ምክንያትም ይሄ ሊሆን ይችላል።
በስምምነቱ የኢራን ሉዓላዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በሆርሙዝ የባሕር መተላለፊያ ላይ የተጣለው ክልከላ ተነስቷል። ማዕቀቦች የሚላሉበት ዕድል ሰፊ እንደሆነም ተመልክቷል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጃትባ ኻሜኒ ለስምምነቱ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል። ኃላፊነቱን የሚወስደውም የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ይሆናል።
አወዛጋቢ የሚሆነው የኢራን የበለጸገ ዩራኒየም ጉዳይ ነው። ኢራን ዩራንየም ማበልጸግን ብቻ ሳይሆን የኒውክሌር ተቋማቷን መልሶ መገንባትንም ወደ ድርድሩ ልታመጣ የምትችለው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብታ እንደሚሆን ይታመናል።
ይህም የኢራንን መሪዎች፣ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ አባላት እና ምክር ቤቱን አጣብቂኝ ውስጥ ይከትታል።
የኒውክሌር ተቋማትን በተመለከተ የሚደረሰው ስምምነት የኢራን አመራሮች ስምምነቱን እንደ ድል አድርገው ከማቅረባቸው ጋር ይቃረናል።
አማካይ መንገድ አለማግኘት ግን የበለጠ ለአደጋ ያጋልጣል።
ኢራን የበለጸገ ዩራኒየሟ ከይዞታዋ እንዲወጣ ካልፈቀደች የተኩስ አቁሙ ስጋት ውስጥ ይወድቃል።
አሜሪካ እና እስራኤል እንደሚሉት ኢራን ስምምነቱን የፈረመችው ጊዜ ለመግዛት ነው። ኢራን የበለጸገ ዩራኒየሟ ከይዞታዋ እንዲወጣ የማትፈቅድ ከሆነ የአሜሪካ እና እስራኤል መከራከሪያ ነጥብ ይጠናከራል።
ከአሜሪካ ጋር ለተደረሰው ስምምነት ዋነኛ ተደራዳሪ የነበሩት የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጊር ጋሊባፍ "ዲፕሎማት አይደለሁም። አሜሪካ ነገሩ እንዲገባት ማድረግ ግን እችላለሁ" ብለዋል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ በበኩላቸው ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ቢደርሱም "የተለየ ዕይታ" እንዳላቸው ገልጸዋል።
ስምምነት ላይ እንዲደረስ የፈቀዱት ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን "የኢራናውያንን ብሔራዊ ጥቅም እንደሚያስጠብቁ" ማረጋገጫ ስለሰጧቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ መሪው እንዳሉት፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ተስፋ በመቁረጣቸው ሁሉንም አማራጭ እየተጠቀሙ" ስለነበረ ስምምነቱ ተፈርሟል።
በቀጣይ በየሁለቱ አገራት መሪዎች በአካል ተገናኝተው ድርድር እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
የመግባቢያ ሰነዱ ላይ መስማማት "የጠላትን አቋም መቀበል" ማለት እንዳልሆነ ጠቅላይ መሪው አክለዋል።
ንግግራቸው ለስምምነቱ ስኬት ዕውቅናውን አግኝቶ ቢከሽፍ ኃላፊነት ከመውሰድ የሚያርቃቸው ይመስላል።
ስምምነቱን በኢራን ውስጥ ያሉ መሪዎች እንዲቀበሉት ከማድረግ ጎን ለጎን በአሜሪካ በኩልም አቋማቸው እውቅና እንዲሰጠው ያደርጋል።
ሁለቱ አገራት የደረሱበት ስምምነት በአውሮፓውያኑ 2015 ከተፈረመው የኒውክሌር ስምምነት ጋር እየተነጻጸረ ነው።
ትራምፕ አገራቸውን ከዚህ ስምምነት ማስወጣታቸው አይዘነጋም።
አሁን የተፈረመው ስምምነት ኢራን ከማዕቀቦች እፎይታ እንድታግኝ የሚያደርግ እና በምጣኔ ሃብት ረገድም የሚጠቅማት እንደሆነ የገለጹም አሉ።
የ2015 ስምምነት ሲፈረም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሐሴን ሮሀኒ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር በሚጎዳ መልኩ ተደራድረዋል በሚል ከፍተኛ ወቀሳ ገጥሟቸዋል።
አሁን ደግሞ ፕሬዝዳንቱ እና አፈ ጉባዔው ኢራንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት እንደሆነ እየገለጹ ነው።
ኢራን በስምምነቱ ጊዜ ከመግዛት በተጨማሪ ከወታደራዊ ጫናም እፎይታ አግኝታለች።
ሆኖም ግን የመጨረሻ ስምምነት ነው ማለት ግን አይደለም። ዋሽንግተን ያሉባትን ኃላፊነቶች በመዘርዘር እና አሁን ያለውን የኢራን አስተዳደር ተጠቃሚ ያደርጋታል።
በመጀመሪያው ዙር ኢራን አሸናፊ ሆና የወጣች ቢሆንም ቀጣዩ ዙር ፈታኝ ይሆናል።
ኢራን ፍላጎቷን አሳልፋ የሰጠች ሳይመስል በድርድር ስምምነቶች ላይ በመድረስ የአገር ውስጥ ጥያቄዎችን መመለስ ይጠበቅባታል።
ቀጣዮቹ 60 ቀናት ኢራን እንደ ድል በገለጸችው ስምምነት እና በእውነታው መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳዩ ይሆናሉ። ስምምነቱ ዳግመኛ ወደ ጦርነት ከመመለስ የሚያቅብ መሆኑም በቀጣይ የሚታይ ነው።
ኢራን የፖለቲካ ልሂቃኗን ጥያቄ ባማከለ መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርጋት የመጨረሻ ስምምነት ላይ የምትደርስ ከሆነ የሚታየው በመጪው ጊዜ ነው።
ከጦርነቱ በፊት በአሜሪካ የተከሰተው የምጣኔ ሃብት መዋዠቅ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲመረጡ ማድረጉ ሲገለጽ ቆይቷል።
በኢራን ጦርነት ወቅት አሜሪካውያን ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። ትራምፕ በጦርነቱ ምክንያት ፖለቲካዊ ዋጋ ሊከፍሉም ይችላሉ።
ሪፐብሊካኖች በተራዘመ ጦርነት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች እየተወቀሱ ይገኛሉ። ስምምነቱ ለትራምፕ እና የፖለቲካ አጋሮቻቸው እፎይታ የሚሰጥ ይሆናል።
ሆኖም ግን ሪፐብሊካኖችን ጨምሮ የአሜሪካ ፖለቲከኞች፤ ዋሽንግተን በስምምነቱ ምን ያህል አትራፊ ነች ብለው ጥያቄ አንስተዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው "ለኢራን 300 ቢሊዮን ዶላር አይሰጥም፤ ሐሰተኛ ዜና ነው" ብለዋል።