ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢቦላ ተይዛ ከምትታከምበት ሆስፒታል የተጠለፈችው የ6 ዓመት ሕጻን ተገኘች
በኢቦላ ተይዛ በሕክምና ላይ ሳለች ከእናቷ ጋር ከሆስፒታል ተጠልፋ የተወሰደችው የስድስት ዓመት ሕጻን መገኘቷን እና "በደህና ሁኔታ" ላይ እንደምትገኝ የጤና ባለሥልጣናት ለቢቢሲ አስታወቁ።
ከቀናት በፊት በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ሕክምና ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሉባምቦ ማቦኮ ጋስተን ሕጻኗ እና እናቷ "በጣም የተቆጡ" ባሏቸው እና ስለት በታጠቁ ሰዎች የኢቦላ ሕክምና ከሚሰጥበት ሆስፒታል መወሰቸዳውን ተናግረዋል።
ሰዎቹ እናት እና ልጅን ያውቁ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፤ ነገር ግን በኢቦላ የሕክማና ማዕከላት ላይ በአካበቢው ሕብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬ እና ፍርሃት አለ።
ሕጻኗ እና እናቷ ከሆስፒታሉ በኃይል ከተወሰዱ ከቀናት በኋላ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ የኢቦላ ሕክምና ማዕከል መምጣታቸውን ዶክተሩ ተናግረዋል።
በዲሞክተቲክ ኮንጎ ውስጥ አሁን ከተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሕክምና ማዕከላቱ በተደጋጋሚ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። እስካሁን 890 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተነገረ ሲሆን፣ ከ230 በላይ ሕይወታቸው አልፏል።
በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የኢቦላ ሕክምና ማዕከላትን ጥሰው በመግባት የሞቱ ዘመዶቻቸውን አስከሬን ለመውሰድ በሚደረግ ሙከራ በሽታው የበለጠ እንዳይስፋፋ ስጋት ተፈጥሯል።
ቀደም ሲል አስከሬን ለመውሰድ በተደረገ ሙከራ በተፈጠረ ግርግር ወቅት ፖሊስ ወደ ሰማይ ጥይት በመተኮስ የተቆጡ ሰዎችን የበተነ ሲሆን በሌላ ስፍራ ደግሞ አስከሬን ለመውሰድ የተከለከሉ ሰዎች የማገገሚ ማዕከልን ድኖኳኖች አቃጥለዋል።
በኢቦላ ምክንያት የሞተ ሰው አስከሬን በሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ የማስፋፋት አቅም ስላለው ቀብር በጥንቃቄ ካልተፈጸመ ሌሎች ሰዎችን በበሽታው ሊያዙ ይችለሉ።
በገጠሩ አካበቢ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ኢቦላ የውጭ ሰዎች የፈጠሩት ነገር እንጂ የለም የሚል አመለካከት መኖሩን የሚናገሩት ፖለቲከኛ ሉክ ማሌምቤ ተገቢው ግንዛቤ መሰጠት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ምንም እንኳን በበሽታው ምክንያት ሰዎች እየሞቱ እና እየታመሙ ቢሆንም ነዋሪዎች "መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሆስፒታሎች ገንዘብ ለማግኘት የፈጠሩት ነው የሚል አሳዛኝ ግንዛቤ አለ" ብለዋል ፖለቲከኛው።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣን አርብ ዕለት እንደተናገሩት በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በሽታው "በፍጥነት እየተዛመተ ነው" በማለት አስጠንቅቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ኃላፊ ማሪ-ሮዝሊን ቤሊዛየር ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት "ወረርሽኙ አሳሳቢ" መሆኑን በመጥቀስ "ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ግን በየዕለቱ እየተጠናከረ ነው" ብለዋል።
ጨምረውም አስከላሁን 75 የጤና ባለሙያዎች በወረርሽኙ ሲሆን ከመካከላቸውም 17 ሕይወታቸ ውአልፏ።ል