ቀጥታ, ትራምፕ ከኢራን ጋር የተስማሙባቸውን ነጥቦች ከአርብ በፊት ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ ተባለ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነቱን ለማቆም የተስማሙባቸውን ነጥቦች ከአርብ በፊት ይፋ ሊያደረጉ እንደሚችሉ ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ተናገሩ። ትራምፕ ስምምነቱ መፈረሙን ተናግረው የነበረ ሲሆን አርብ በስዊዘርላንድ የሁለቱ አገራት ልዑካን በአካል ተገናኝተው ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ እየተነገረ ነው። ጄዲ ቫንስ የመግባቢያ ሰነዱ “አንድ ገጽ ከግማሽ” እና “በጣም ጥቅል” ሰነድ መሆኑን ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከስምምነቱ በኋላ የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የአሜሪካን እገዳ ማለፋቸውን መረጃዎች አመለከቱ

    በዚህ ሳምንት ዋሺንግተን እና ቴህራን ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ካሳወቁ በኋላ ቢያንስ ሦስት የኢራን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የአሜሪካን እግድ አልፈው ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ መሄዳቸውን መረጃዎች አሳዩ።

    የመርከቦቹ እንቅስቃሴ ኢራን ወደ ውጪ የምትልከውኘ ነዳጅ ቀስ በቀስ መጀመሯን ያሳያል ተብሏል።

    ግዙፍ የነዳጅ ጫኝ የሆኑት ሄሮ II እና ዲዮና እያንዳንዳቸው 2 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ጭነው የኦማን ባሕረ ሰላጤን አልፈው ወደ ምሥራቅ መቅዘፋቸውን የመርከቦችን መረጃ የሚከታተሉ ሁለት ድርጅቶች ይፋ አድርገዋል።

    ሴዌዝማክስ ሶኒያ I የተባለችው እና 1 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫነች መርከብ እንዲሁ የአሜሪካ ባሕር ኃይል እገዳን አልፋ ወደ ሲንጋፖር ማምራቷን መረጃዎቹ ጠቁመዋል።

    ሄሮ II ነዳጁን የጫነችው በመጋቢት የመጨረሻ ሳምንት ሲሆን፣ ዲዮና እና ሶኒያ I ደግሞ በሚያዚያ ወር መጀመርያ ሳምንት ላይ መጫናቸውን የኬፕለር መረጃ ያሳያል።

    የአሜሪካ ባሕር ኃይል ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦች ላይ ክልከላ በማድረጉ ቴህራን ወደ ውጭ የምትልከውን ነዳጅ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ቆይቷል።

    ኢራን በግንቦት ወር ወደ ውጭ የላከችው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ከባለፉት ስድስት ዓመታት አንጻር ሲተይ በጣም ዝቅተኛ ነው።

    በግንቦት ወር በየቀኑ 260,000 በርሜል ነዳጅ ብቻ ትልክ እንደነበር ኬፕለር ይፋ አድርጓል።

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ሲስማሙ እገዳው እንደሚነሳ እና የነዳጅ ምርቷን ወደ ውጪ ለመላክ እንደምትችል መግባባታቸውን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ማክሰኞ ዕለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

  2. የኢራን ስምምነት የ300 ቢሊየን ዶላር ፈንድን እንደሚያካትት እና ከግማሽ በላዩ መከፈሉን ምንጮች ለሮይተርስ ተናገሩ

    በአሜሪካ እና በኢራን የስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ በቴሀራን ያለውን ኢንቨስትመንት ለማንቀሳቀስ በሚል 300 ቢሊየን ዶላር መቀመጡን እና ከግማሽ በላይ የሚሆነው መሰጠቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሮይተርስ ተናገሩ።

    አርብ ዕለት የሚፈረመው ስምምነት የያዛቸው ዝርዝር ሃሳቦች ይፋ ባለመሆናቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ምንጮች ገንዘቡ የተቀመጠው ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችላቸው የመጨረሻ ስምምነት ለመድረስ እንዲችሉ በሚል የምጣኔ ሃብት ማበረታቻ መሆኑን ገልጸዋል።

    ከዚህ ቀደም ሮይተርስ ለኢራን ስለሚሰጥ ገንዘብ የዘገበ ቢሆንም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን አስተባብለዋል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት እሁድ ዕለት ጦርነቱን ለማስቆም በሚያችል ማዕቀፍ ላይ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ቴህራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ በምላሹ ኢራን የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለቸ።

    አዲሱ ፈንድ የግል ኢንቨስትመንት ማሳለጫ እንደሚሆን እና ምንም ዓይነት የመንግሥት ገንዘብን እንደማያካትት ተገልጿል።

    አክለውም ገንዘቡን ለመስጠት መቀመጫቸውን አሜሪካ፣ የአረብ ሰላጤ አገራት፣ እስያ፣ ደቡብ አሜሪካ እና አፍሪካ የሚገኙ ኩባንያዎች ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

    ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈስሱት በኢነርጂ፣ ሎጀስቲክ፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ትራንስፖርት ላይ መሆኑን ምንጮች ጨምረው ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    የመልሶ ግንባታ እና የልማት ፈንድ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል በተባለው ፈንድ የቀጣናው አገራት በተለያዩ መንገዶች እንዲያዋጡ ይደረጋል ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል።

    ይህም በብድር፣ ቀጥታ በጦርነት የወደሙ ቦታዎችን እና መሠረተልማቶችን መልሶ መገንባት ላይ መሳተፍ ይገኝተበታል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገራት መካከል ኢራን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ናት።

    ባለፉት አራት አስርት ዓመታት አንድም የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ኢራን ያልመጣ ሲሆን የዓለም አቀፍ እና የአሜሪካ ማዕቀቦችም ሃብቶቿን እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል።

    ኢራን በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ግዙፍ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት ስትሆን በነዳጅ ዘይት ክምችትም አራተኛዋ ናት።

  3. ትራምፕ ከኢራን ጋር የተስማሙባቸውን ነጥቦች ከአርብ በፊት ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ ተባለ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነቱን ለማቆም የተስማሙባቸውን ነጥቦች ከአርብ በፊት ይፋ ሊያደረጉ እንደሚችሉ ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ተናገሩ።

    ትራምፕ ስምምነቱ መፈረሙን ተናግረው የነበረ ሲሆን አርብ በስዊትዘርላንድ የሁለቱ አገራት ልዑካን በአካል ተገናኝተው ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ እየተነገረ ነው።

    ጄዲ ቫንስ የመግባቢያ ሰነዱ “አንድ ገጽ ከግማሽ” እና “በጣም ጥቅል” ሰነድ መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስለስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች መናገር ጀምረዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ስምምነቱ በጄኔቫ በሚፈረምበት ዕለት አርብ ዳግም ይከፈታል ተብሏል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ከአሜሪካ ጋር ዘላቂ ሰላም ላይ ለመድረስ የሚደረገው አዲሱ ዙር ውይይት በዚያው ዕለት ስዊትዘርላንድ ውስጥ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

    ለቡድን ሰባት አገራት ስብሰባ ፈረንሳይ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ማክሰኞ ዕለት ከግብጽ፣ ኳታር እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ መሪዎች ጋር ተገናኝተው በኢራን ዙሪያ መክረዋል።

    ሰኞ ዕለት ትራምፕ ከፈረንሳዩ ፕሬዚፈዳንት ኢማኑዔል ማክሮን ጋር ሲነጋገሩ “ተፈርሟል ብዬ ስነግራችሁ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ስምምነቱ ተፈርሟል” ብለው ነበር።

    የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስምምነቱ የትራምፕ፣ የምክትላቸው ቫንስ እና የኢራን የፖርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ ኤሌክትሮኒክስ ፊርማ ተቀምጦበታል ብለዋል።

    በዚህ ሳምንት የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ላይ እንዲሁም በኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም ላይ መነጋገር ይጀመራል ተብሏል።

    ኢራን ላይ የተጣሉትን ማዕቀቦች ለማንሳት ወይም እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ ሃብቶቿን ለመልቀቅ ኢራን ለስምምነቱ ያላት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።

    ቫንስ ለኤንቢሲ እንደተናገሩት በስምምነቱ መሠረት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ወደ ኢራን መግባት አለበት ብለዋል።

    “የስምምነቱ አንኳር ነጥቦች ከሆኑት መካከል አንዱ [ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ] እና ዩናይትድ ስቴትስ በከፍተኛ ሁኔታ ተብላልቶ የተቀመጠውን ዩራኒየም እንድታስወግድ እንደሚደግፉ በግልጽ ተቀምጧል።”

    ትራምፕ የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች አርብ ዕለት ከተፈረሙ በኋላ ይፋ ይሆናሉ ብለው የነበረ ቢሆንም ቫንስ ግን ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ከዚያ በፊት ይፋ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

    ቫንሰ ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታም ሰነዱ ጥቅል መሆኑን እና በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች ወደፊት በሚደረጉ ንግግሮች መግባባት ላይ ሊደረስባቸው ይገባል ብለዋል።

  4. ጄዲ ቫንስ "የአሜሪካ ሰባራ ሳንቲም ወደ ኢራን አይሄድም” አሉ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባደረገቸው ስምምነት የተነሳ “ሰባራ ሳንቲም” ወደ ቴህራን አይሄድም ሲሉ ተናገሩ።

    ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለኢራን “ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብ ሰጥተዋል” ሲሉ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር አነጻጽረዋቸዋል።

    ኳታር 300 ቢሊዮን ዶላር ለኢራን ትሰጣታለች እንዲሁም 24 ቢሊየን እንዳይንቀሳቀስ የተደረገ የቴህራን ሃብት ይለቀቃል ስለተባለው ሲጠየቁ ቫንስ “በመሠረቱ ይህ የኢራናውያን ፕሮፓጋንዳ ነው” ብለዋል።

    “እየሆነ ያለው የተወሰኑ ግለሰቦች ለአገር ውስጥ ማኅበረሰብ ስምምነቱ በጎ እንደሆነ በተቻለ መጠን ለማሳየት እየሞከሩ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    “የአሜሪካ ሰባራ ሳንቲም ወደ ኢራን አይሄድም። 300 ቢሊዮን ዶላር ወይም 24 ቢሊዮን ዶላር ምንም ዓይነት ገንዘብ”

    ይሁን አንጂ “ግዴታቸውን የሚወጡ ከሆነ ለኢራን ጥቅም አለው” በማለት ኳታር፣ ዩኤኢ ወይም ሳዑዲ አረቢያ በኢራን መዋዕለ ነዋያቸውን ሊያፈሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

  5. ‘ኢራን [ስምምነቱ] ቶሎ እንዲጠናቀቅ ትፈልጋለች”-ዶናልድ ትራምፕ

    በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ፈረንሳይ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያካሄዱት ሁለተኛው ዙር ድርድር “ጊዜውን ጠብቆ ይሄዳል” ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ።

    “ኢራን በቶሎ እንዲጠናቀቅ ትፈልጋለች፤ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ ይፈልጋሉ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ስምምነቱ ይፋ ለምን እንደማይሆን ሲጠየቁ “መጀመሪያ በይፋዊ መፈራረሙ እንዲቀድም” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

    “ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አይኖራትም፤ ያንን ነው የሚለው. . . ያ ነው 99.9 በመቶ የምፈልገው የነበረው”

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ከ60 ቀናት በኋላም “ያለምንም ክፍያ” ክፍት ይሆናል ሲሉም አብራርተዋል።

    ትራምፕ ስምምነቱን “ቃል በቃል” ለማንበብ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚጠሩም ጨምረው አስረድተዋል።

    “ምክንያቱም በጣም ወሳኝ ሰነድ ነው” ሲሉ አክለዋል።

    ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አይኖራትም ካሉ በኋላ “እውነቱን ለመናገር ሌላው አስፈላጊ አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

    ስምምነቱን “ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ በተቃራኒ የቆመ ግድግዳ” ሲሉ ገልጸውታል።

    የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከኢራን ጋር ካደረጉት ስምምነት ጋር በማነጻጸርም “መካከለኛው ምሥራቅን ሊያጠፋ ይችል ነበር” ብለዋል።

    የተብላላውን ዩራኒየም ከኢራን ያወጡ እንደሆን ሲጠየቁም፣ መቼ ይወጣል የሚለው ላይ ምንም ጥድፊያ እንደሌለ ተናግረዋል።

    ትራምፕ ስምምነቱ እንዲጸድቅ ወደ ኮንግረስ እንደሚላክ ጨምረው አስረድተዋል።

  6. ሄዝቦላህ፣ ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ድርድር እስራኤል ከሊባኖስ እንድትወጣ ለመጠየቅ ቃል መግባቷን ገለጸ

    ሄዝቦላህ ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ቀጣይ ድርድር የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስን ለቅቀው እንዲወጡ እንደምትጠይቅ ማረጋገጫ ማግኘቱን አስታወቀ።

    የሄዝቦላህ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው ስምምነት አርብ ዕለት ከተፈረመ በኋላ በሚደረገው ንግግር የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ ለቅቆ መውጣት ይኖርበታል ብሏል።

    ቡድኑ ለሮይተርስ “እስራኤል [ከሊባኖስ] ለቅቃ እስካልወጣች በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የኒውክሌር ስምምነት አይኖርም” ሲል ተናግሯል።

    የሄዝቦላህ ዋና ፀሐፊ ናኢም ቃሴም ለኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ቡድኑ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ባለው አል ማናር ቴሌቪዢን ጣቢያ ቴሌግራም ገጽ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት ቃል አቀባዩ ለሊባኖስ ስላሳዩት “ጠንካራ አቋም እና አጋርነት” አመስግነዋል።

    አክለውም እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻዋን እንድታቆም በኢራን እና አሜሪካ ስምምነት ውስጥ “መሠረታዊ አንቀጽ” ሆኖ እንዲገባ በማድረጋቸው አመስግነዋቸዋል።

  7. በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ ማን ምን አለ?

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት በጥሩ ሁኔታ ላይ በመሄድ “ወደ ሁለተኛ ደረጃ ደርሷል” ቢሉም ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ከሦስት ወራት በላይ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም ከስምምነት የተደረሰው እሁድ ዕለት ቢሆንም አስካሁን ሙሉው የስምምነት ዝርዝር ይፋ አልሆነም።

    ሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ስምምነቱ ተፈርሟል” በማለት ዝርዝሩ “በጣም በቅርቡ” ሙሉ ለሙሉ ይፋ ይሆናል ብለው ተናግረው ነበር።

    ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ስምምነቱ ሁለቱ ወገኖች በይፋ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ከፈረሙት በኋላ ይፋ ሊደረግ እንደሚችል ጨምረው ገልጸዋል።

    የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዳሉት በተደረሰው ስምምነት መሠረት የሆርሙዝ ወሽመጥ አርብ ዕለት ሙሉ ለሙሉ ክፍት ይደረጋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ የስምምነቱን ይዘት ቀደም ብለው ይፋ እንዲደረግ ሊወስኑ ይችላሉ ብለዋል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ደግሞ የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሲፈረም እዚያው የመጨረሻውን ስምምነት ለማድረግ የሚያስችል ድርድር እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዙሪያ የሚካሄደው የቴክኒክ ንግግር በዚህ ሳምንት በሚካሄደው ድርድር ወቅት ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

  8. የኢራን ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ “በጣም መጨቆኑን” አሠልጣኙ ተናገሩ

    የኢራን ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አሚር ጋሌኖይ በዓለም ዋንጫ ቡድናቸው “በጣም መጨቆኑን” ተናገሩ።

    ከኒው ዚላንድ ጋር ሁለት አቻ መውጣታቸውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ከሁሉም የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ አገራት የኢራን ቡድን “መጨቆኑን” ገልጸዋል።

    ተጫዋቾቹ በመጨረሻው ሰዓት የጉዞ ክልከላ እንደተጣለባቸው አሠልጣኙ ተናግረዋል።

    ከኒው ዚላንድ ጋር ከተጋጠሙ በኋላ በሎስ አንጀለስ ቆይተው ማረፍ ቢፈልጉም በአፋጣኝ ሜክሲኮ ወደሚገኘው የሥልጠና ማዕከል እንዲመለሱ ትዕዛዝ መተላለፉን አስረድተዋል።

    መጀመሪያ ላይ በተያዘው ዕቅድ መሠረት የዓለም ዋንጫ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የኢራን ብሔራዊ ቡድን በአሪዞና ይቆያል ተብሎ ነበር። ኋላ ላይ ግን ወደ ሜክሲኮዋ ቲጁአና እንዲዛወሩ ተደርጓል።

    “ጨዋታው እንዳለቀ ‘ውጡ’ አሉን። አውሮፕላን ተሳፍረን ቲጁአና እንድንሄድ ተነገረን። በዚህም በጣም ተረብሸናል” ብለዋል።

    አሠልጣኙ አክለውም “ቀድመን እንድንሄድ እያስገደዱን ነው። ነገሮችን የበለጠ አክብደዋቸዋል። ነገር ግን በእነሱ ምክንያት ቡድናችን ምርጥ ከመሆን ወደኋላ አይልም” ሲሉ ተናግረዋል።

  9. “በሊባኖስ ላይ የሚፈጸም የእስራኤል ጥቃት ከአሜሪካ ጋር የተደረገው ስምምነት ጥሰት ነው” ኢራን

    ከዚህ በኋላ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው የትኛውም ዓይነት ጥቃት ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት የሚጥስ ነው ስትል ኢራን አስጠነቀቀች።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እንዳሉት ስምምነቱ ሲደረስ በአንድ በኩል ኢራን እና ሄዝቦላህ በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካ እና እስራኤል ሆነው ነው በማለት የእስራኤል ጥቃት እንዲቆም አሳስበዋል።

    አራግቺ አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት "በሊባኖስ ያለው ጦርነት ማብቃት ከአጠቃላዩ ጦርነት ማብቃት ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፣ የጦርነቱ ማብቃት በተጨማሪም የወረራ ማብቃትንም የሚያካትት ነው” ብለዋል።

    በዚህም መሠረት “ከዚህ በኋላ የእስራኤል ወረራ በሊባኖስ መሬት ላይ የሚቀጥል ከሆነ የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት ጥሰት ነው ብለን በእኛ በኩል እንመለከተዋለን” ሲሉ አራግቺ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ንግግር የተሰማው እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ወደሚገኙ ወታደሮቿ እየተጠጉ ነበር ያለቻቸው “ሽብርተኞች” ላይ ጥቃት መፈጸሟን ካሳወቀች በኋላ ነው።

    የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ቡድን በበኩሉ ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን ማስወንጨፉን ተናግሯል።

    አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት መድረሳቸው ይፋ ከሆነ በኋላ እስራኤል “የደኅንነት ቀጣና” ባለችው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ ኃይሎቿ እንደሚቆዩ አሳውቃለች።

    በርካታ የእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት አውግዘውታል።

  10. አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

    አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለኢራን መልሶ ግንባታ ይሰጣል መባሉን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተባበሉ።

    ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፈጽሞ እንደማይኖራት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰው፤ ነገር ግን አሜሪካ ለኢራን 300 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ተስማምታለች የሚሉ ዘገባዎችን አስተባብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "አሜሪካ ለኢራን 300 ሚሊዮን ዶላር ልትከፍል ነው በሚል የሚነገረው በደደብ ዲሞክራቶች የሚነገር ሐሰተኛ ዜና ነው” ብለዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ ደረሱበት የተባለው እና እራሳቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፈርመውበታል የተባለው ጦርነቱን የሚያስቆመው የመግባቢያ ሰነድ ዝርዝር ዋነኛው ይዘት ይፋ አልሆነም። ነገር ግን ከኢራን እና ከአሜሪካ በኩል እየወጡ ያሉ የስምምነቱ ይዘቶች ላይ አንዳንድ ልዩነቶች እየታዩ ነው።

    ሁለቱም አገራት ከርቀት በኤሊክትሮኒክ መንገድ ተቀብለው የፈረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ሙሉ ለሙሉ የተቀበሉት ሲሆን፣ የመጨረሻው ስምምነት አርብ ዕለት ስዊትዘርላንድ በተወካዮቻቸው አማካይነት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።

  11. የኢራንን ጦርነት የሚያስቆመው ስምምነት እንደተፈረመ፣ ዝርዝሩም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ትራምፕ አስታወቁ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ጦርነት የሚያስቆመው ስምምነት እንደተፈረመ እና ዝርዝሩም ይፋ እንደሚደረግ አስታወቁ።

    የስምምነቱ ዝርዝር ይፋ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፤ ይፋዊ ፊርማ የማኖር ሥነ ሥርዓቱ የፊታችን አርብ በጄኔቫ የሚከናወን ይሆናል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው “ትግሉ አላከተመም” ብለዋል። አገራቸው አሁንም በተጠንቀቅ እንደቆመች እና በደቡብ ሊባኖስ “ከውጊያ ነጻ የሆነ ቀጣና” እንደሚኖራት ገልጸዋል።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን ስምምነቱ በአግባቡ ከተተገበረ ለኢራን “የሚያኮራ ሰነድ” ነው ማለታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደተናገሩት የመግባቢያ ስምምነቱ መፈረሙን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ “በአፋጣኝ” ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።

    በስምምነቱ መሠረት በሊባኖስ “ወታደራዊ ዘመቻ” መቆም እንዳለበት ተገልጿል። የሊባኖስ ባለሥልጣናት ተፈናቃዮች የአካባቢው ደኅንነት ሳይረጋገጥ እንዳይመለሱ ቢያሳስቡም ብዙዎች ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው።

  12. በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም ተባለ

    አሜሪካ እና ኢራን በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም እንደማይጠበቅባቸው የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ገለጹ።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከሲኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ “የሆርሙዝ ወሽመጥ ለረዥም ጊዜ ከክፍያ ነጻ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል።

    ጦርነቱ መነሳቱን ተከትሎ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ለሚያልፉ መርከቦች የክፍያ ሥርዓት ዘርግታ ቆይታለች።

    አሁን ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው ስምምነት አማካኝነት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያለ ክፍያ ማለፍ ጊዜያዊ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ጄዲ ቫንስ፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ከኢራን ጋር መወያየት እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

    ክፍያውን ማስቀረት “በቴክኒክ ድርድሩ ወቅት የምናነሳው ጉዳይ ይሆናል። አብረን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን የምንወያይባቸው በጣም ጠቃሚ ነጥቦች ይኖራሉ” ብለዋል።

  13. የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት በቀጣይ ቀናት እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ማክሮን ገለጹ

    ከሁለት ወይም ከሦስት ቀናት በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ጥምር እንቅስቃሴ እንደሚጀመር የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገለጹ።

    ዛሬ በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሆርሙዝ ወሽመጥን ነጻ እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ “በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ” ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

    የሁለቱ አገራት ጥምር እንቅስቃሴ ወደ አካባቢው ተዋጊ አውሮፕላን እና ፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎችን መላክን እንደሚያካትት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

    “በቀጣናው ተዋጊ አውሮፕላን ጫኙ መርከብ ቻርለስ ደ ጎል አለን። የድጋፍ ቁሳቁስ ጭኗል። ስምምነቱ በተረጋገጠ በሁለት ወይም ሦስት ቀናት ሊሰማራ ይችላል” ብለዋል።

    ስምሪቱ የሚከናወነው ከአሜሪካ እና “በትይዩ ደግሞ ከኢራናውያን ጋር” መሆኑን ማክሮን ጠቅሰዋል። በዚህም የሆርሙዝ ወሽመጥ “በሰላም ተከፍቶ መዝለቁን” ማረጋገጥ እንደሚቻል አክለዋል።

  14. የኒውክሌር መርሃ ግብር እና ተያያዥ ጉዳዮች በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውይይት ይደረግባቸዋል- የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ለማረጋገጥ እና የፊታችን አርብ በስዊትዘርላንድ ስለሚደረገው ይፋዊ የፊርማ ሥነ ስርዓት ለብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

    ቴህራን አሜሪካ ላይ ስላላት የአመኔታ ችግር በድጋሚ ገልፀው፤ አገራቸው የአሜሪካን ቃል ኪዳኖች አፈፃፀም “እንደምትከታተል” ጠቅሰዋል።

    እስራኤል ቤይሩትን ማጥቃቷን ተከትሎ ቴህራን መዛቷ “የስምምነቱን ይዘት እንዲፋጠን ያገዘ እና አንዳንድ ጉዳዮችን የፈታ” እንደነበር ጠቁመዋል።

    ምክትል ሚኒስትሩ ኢራን ድርድሩ በ60 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላት ተናግረዋል። በኢራን ላይ የተጣሉ ሁሉም ማዕቀቦች እንዲነሱ እና ከአገሪቱ የኒውክሌር መርሃ ግብር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ድርድር ከሚደረግባቸው ጉዳዮች ውስጥ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

    በዚህ 60 ቀናት ውስጥ ጦርነቱን ተከትሎ ጉዳት የደረሰበትን የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ዳግም ለመገንባት የሚያስችሉ ጉዳዮችም የድርድሩ አካል ናቸው ብለዋል።

  15. ኢራን፤ እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መቆም አለበት” አለች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ዛሬ ሰኞ ማለዳ ከቱርክ፣ ከኢራቅ እና ከግብፅ አቻዎቸው ጋር በስልክ መወያየታቸውን በቴሌግራም ገጻቸው ላይ አስታወቁ።

    አራግቺ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ጋር እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መቆም እንዳለበት” መወያየታቸውን አስፍረዋል።

    አራግቺ አክለውም ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የአሜሪካ ኃላፊነት እንደሆነም ገልጸዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ አገራቸው ጦሯን የደኅንነት ቀጣና ብላ ከከለለችው ደቡባዊ ሊባኖስ፣ ጋዛ እና ሶሪያ እንደማታስወጣ አስታውቀዋል።

    ኢራን በሊባኖስ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነም አገራቸው “ሙሉ ኃይሏን ተጠቅማ” ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።

    ካትዝ በደቡባዊ ሊባኖስ ያለው የደኅንነት ቀጣና ከአካባቢው ነዋሪዎች እና “ከሁሉም የሽብር መሠረተ ልማቶች፣ በመንደሩ ከሚገኙ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቤቶች” ነጻ እንደሚሆን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

  16. የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ያለ ጊዜ ገደብ ለመቆየት እንደሚያስብ ሚኒስትሩ ገለጹ

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሊባኖስ ያለምንም የጊዜ ገደብ የመቆየት ሃሳብ እንዳለው ሚኒስትሩ እዝራኤል ካትዝ አስታወቁ።

    ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት አሜሪካ እና ኢራን አደራዳሪዋ ፓኪስታን ባቀረበችው የመግባቢያ ሰነድ ላይ መስማማታቸውን ተከትሎ ነው።

    ሁለቱ አገራት“የትኛውንም ወታደራዊ ዘመቻዎች፣ በሊባኖስ ጨምሮ” ለማቆም ተስማምተዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በሂብሩ በጻፉት መግለጫ ጦራቸው ከሊባኖስ ይውጣ የሚለውን “ግልጽ በሆነ እና በሚጠበቁ ጫናዎች የተነሳ” ይቃወማል ብለዋል።

    መከላከያ ሚኒስትሩ ከቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ጦሩ በሊባኖስ፣ በሶሪያ እና ጋዛ “የደህንነት ቀጣናዎች ያለ ጊዜ ገደብ” እንደሚቆይ መነጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

    አክለውም “ሁሉም የሽብር መሠረተ ልማቶች”፤ “የእስራኤልን ድንበሮች ለመከላከል” ይወድማሉ እንዲሁም ይህንን አቋሟን ለአሜሪካ ማሳወቋን ገልጸዋል።

    “ኢራን በሊባኖስ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጥቃት ከፈጸመች ሙሉ ኃይላችንን ተጠቅመን ጥቃት እንፈጽማለን። ያለንንም የመከላከያ የበላይነት እናሳያለን።”

  17. ሊባኖስ ከአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ስምምነት በኋላ ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ለመመለስ እንዳይቸኩሉ አስጠነቀቀች

    የደቡብ ሊባኖስ ባለሥልጣናት በሦስት ወሩ የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ውጊያ የተፈናቀሉ ሰዎች ሰኞ ዕለት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ለመመለስ እንዳይጣደፉ አስጠነቀቁ።

    ባለሥልጣናቱ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት እስራኤል ጦሯን ከደቡባዊ ሊባኖስ እንደማታስወጣ በመናገሯ ነው።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን በማስወንጨፉ በደቡባዊ ሊባኖስ ከፍተኛ አየር ድብደባ አካሄዳለች።

    እስራኤል በሊባኖስ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 3,700 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ 1.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራንን የምታሸማግለው ፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ አገራቱ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት “ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች የሚደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎች በቋሚነት እና አሁኑኑ እንዲቆሙ” መግባባታቸውን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር በተቆጣጠሯቸው የደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢዎች የሚገኙ አስተዳዳሪዎች ነዋሪዎች እንዳይመለሱ ማስጠንቀቃቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ አገራቸው ጦሯን የደህንነት ቀጣና ብላ ከከለለችው ደቡባዊ ሊባኖስ፣ ጋዛ እና ሶሪያ እንደማታስወጣ ገልጸው፣ ኢራን በሊባኖስ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

    ካትዝ በደቡባዊ ሊባኖስ ያለው የደህንነት ቀጣና ከአካባቢው ነዋሪዎች እና “ሁሉም የሽብር መሠረተ ልማቶች፣ በመንደሩ የሚገኙ [ከሄዝቦላህ ጋር] ግንኙነት ያላቸው ቤቶች” ነጻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

  18. ‘በዚህ ስምምነት እኛ አጋሮች አይደለንም፤ እኛን አይገዛም’- የእስራኤል ሚኒስትር

    እሁድ ምሽት በፓኪስታን ይፋ በተደረገው የአሜሪካ እና የኢራን የስምምነት ማዕቀፍ ላይ እስራኤል ይፋዊ አስተያየት እስካሁን አልሰጠችም።

    ዛሬ ሰኞ ጠዋት ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ብሔራዊ የደኅንነት ሚኒስትር ኢትማር ቤን-ጋቪር ግን አስተያየት ሰጥተዋል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገውን ስምምነት በመተቸት “ደኅንነታችን በማያስጠብቀው በዚህ ስምምነት እኛ አጋሮች አይደለንም። እናም በየትኛውም መንገድ እኛን እይገዛም” ብለዋል።

    እስራኤል “ሄዝቦላህን ከመበታተን ያነሰ ነገር መቀበል የለባትም” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ላይ የሚደረገው እርምጃ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

    “እያንዳንዱ ከእስራኤል ወደ ሊባኖስ የሚጓዝ ድሮን፣ ሰው አልባ በራሪ ወይም ሚሳዔል በዳሂያ ጥቃት ይፈጽማል” ሲሉም አክለዋል።

    ቤን-ጋቪር የራሳቸውን መንግሥት በተደጋጋሚ የሚተቹ ሲሆን፤ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት “በፍልስጤም ማኅበረሰብ ላይ ተደጋጋሚ የግጭት ቅስቀሳ” በማድረግ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

  19. የአሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ይፋ ከሆነ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ

    አሜሪካ እና ኢራንን የምታሸማግለው ፓኪስታን ሁለቱ አገራት በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ መስምምታቸውን ይፋ ካደረገች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ።

    ዶናልድ ትራምፕ ከስምምነቱ በኋላ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም ይከፈታል ብለዋል።

    ሰኞ ዕለት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በ4.3 በመቶ ቀንሶ በበርሜል 83.55 ዶላር ተሸጧል።

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት አርብ ሰኔ 12 2018 ዓ.ም. በስዊትዘርላንድ ይፈረማል ብለዋል።

    የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዘም ጋህሪባባዲ ለአገሪቱ ቴሌቪዥን በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከአሜሪካ ጋር ድርድር ሲደረግበት የቆየው ሰነድ ላይ መስማማታቸውን አረጋግጠዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “ነዳጁ መፍሰስ ይጀምር” ሲሉ ጽፈዋል።

    የኢነርጂ ግብይት ተንታኝ የሆኑት ቫንዳና ሃሪ ግን የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ይፋ ባለመሆናቸው “በገበያው ላይ አለመረጋጋር እና እርግጠኝነት ማጣትን ሊያስከትል ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

    አክለውም በዚህ ሳምንት በነዳጅ ገበያው ላይ መዋዠቅን እና እርግጠኛ አለመሆንን ልናይ እንችላለን ብለዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ የተዘጋው አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ የካቲት 21 2018 ኣ.ም. ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው።

    ከጥቃቱ በኋላ ቴህራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በሚያልፍበት ሆርሙዝ በኩል በሚቀዝፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ዝታለች።

    ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    ከግጭቱ በፊት ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በበርሜል 70 ዶላር ይሸጥ ነበር።

    ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በጥቂት ቀናት ይህ ዋጋ ወደ 120 ዶላር ከፍ ብሎ ነበር።

  20. የተባበሩት መንግሥታት እና የተለያዩ አገራት በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አደነቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ ቃል አቀባይ “ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን የሰላም ስምምነቱ ላይ መድረሳቸውን ይፋ በማድረጋቸው” ደስተኛ መሆናቸውን ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ አክለውም “ይህ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ እርምጃ” መሆኑን ገልጸዋል።

    የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱን ካደነቁ የዓለም መሪዎች መካከል ናቸው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጃፓን “በሆርሙዝ ወሽመጥ ነጻ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ በተግባር እንደሚረጋገጥ በብርቱ ተስፋ ታደርጋለች” ካሉ በኋላ “በኢራን የኒውክሌር እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የመጨረሻው ስምምነት በቅርቡ ይደረሳል” ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒሲትር አንቶኒ አልባኔዝ ስምምነቱ “ቋሚ እና ዘላቂ ሰላም” ያመራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    “ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ ቢወስድም ይህንን ወሳኝ የንግድ መተላለፊያ መልሶ መክፈት በኢነርጂ ዋጋ እና ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ይቃለላል” ብለዋል።

    የኒው ዚላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊንስተን ፒተርስ “ወሳኝ እና ገንቢ ስምምነት” እንዲሁም “ውጥረትን ለመቀነስ እንዲሁም መረካካትን ለዓለም ምጣኔ ሀብት ደኅንነት ወሳኝ በሆነው ቀጣናው ለማምጣት” ቁልፍ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን ከስምምነቱ በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ አሜሪካን እና ኢራንም እንዲሁ በድርድሩ ውስጥ የተሳተፉትን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    “ይህ ቀጣናዊ መረጋጋት ለማምጣት እና ዓለም ምጣኔ ሀብትን ለማረጋጋት ጥሩ ዕድል ነው” ብለዋል።

    ስምምነቱ በፍጥነት እና በተሟላ መልኩ ተግባራዊ አንዲሆን ጥሪ ያቀረቡት አገራቱ የሆርሙዝ ወሽመጥ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ያለገደብ” እንዲከፈት ጠይቀዋል።