ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕፃናት ላይ አካላዊ ቅጣት መፈፀም በትምህርት ውጤታቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጥናት አመለከተ
ሕፃናት ላይ አካላዊ ቅጣት መፈፀም የመጀመርያ ደረጃ ላይ ያላቸው ውጤት እንዲቀንስ ወይም በጉርምስናቸው ወቅት አደገኛ ባሕርይ እንዲያሳዩ ሊያደርግ እንደሚችል ጥናት አመለከተ።
ጥናቱ የተካሄደው በለንደን ኮሌጅ ዩኒቨርስቲ አጥኝዎች ነው።
አጥኝዎቹ አካላዊ ቅጣት የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመመልከት ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2002 ባሉት ዓመታት በዩናይትድ ኪንግደም በተወለዱ እና እድሜያቸው ሦስት፣ አምስት እና ሰባት በሆኑ 19 ሺህ ሕፃናት ላይ ጥናት አካሂደዋል።
በጥናታቸውም "ምንም ይሁን ምን አካላዊ ቅጣት ጥሩ አለመሆኑን" አረጋግጠዋል።
በመሆኑም እንግሊዝ እና ሰሜን አየርላንድ እንደ ስኮትላንድ እና ዌልስ ይህንን የሚከለክል ሕግ እንዲያወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የእንግሊዝ የትምህርት መሥሪያ ቤት መንግሥት በአካላዊ ቅጣት ላይ ያለውን ሕግ የመቀየር እቅድ እንደሌለው ገልጿል።
ሆኖም "የሕፃናት ደኅንነት እና ጤና መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው" ብሏል።
የጥናቱ መሪ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር አንጃ ሄልማን "ጥናቱ አካላዊ ቅጣት ለሕፃናቱ የሚጠቅመው ነገር እንደሌለ እና የሚያስከትለው ውጤት አሉታዊ እንደሆነ ደርሶበታል" ብለዋል።
ቡድኑ በጥናቱ ከተካተቱ 19 ሺህ ሕፃናት መካከል በእንግሊዝ የ7 ሺህ 559 ተማሪዎችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የውጤት ሰርተፊኬት ከሌሎች የአገሪቷ ተማሪዎች ውጤት ጋር አነጻጽሯል።
በዚህም አካላዊ ቅጣት የተፈፀመባቸው ተማሪዎች እንግሊዝኛ እና ሒሳብ ትምህርትን ጨምሮ የማለፊያ ነጥብ ያለማምጣታቸውን እድል በ5.7 በመቶ እንደጨመረው ተመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በልጅነታቸው አካላዊ ቅጣት የተፈፀመባቸው የ14 ዓመት ልጆች አደገኛ በሆኑ ባሕርያት ላይ የመሳተፋቸው ዕድል 33 በመቶ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል።
ሔልማን " በዩናይትድ ኪንግደም አካላዊ ቅጣት እንደሚቆም ተስፋ አለኝ፤ በመሆኑም ሕፃናት ልክ እንደ አዋቂዎች ሁሉ ከአካላዊ ጥቃት ተመሳሳይ ጥበቃ ይኖራቸዋል" ብለዋል።
ጥናቱ የተሰራው አከላዊ ጥቃት የተፈፀመባቸው ተማሪዎች ወላጆች የሞሉትን መጠይቅ በማጠናቀር ነው።
ሆኖም ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት በሕፃናቱ ሕይወት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ምክንያቶች ስላሉ አካላዊ ቅጣት እና ውጤቱ ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የጥናቱ ትንታኔ አያረጋግጥም።
ስኮትላንድ ከ16 ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ላይ አካላዊ ቅጣትን በመከልከል እና ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳይገርፉ የሚያግድ ሕግ በ2020 በማውጣት የመጀመሪያዋ የዩኬ አካል ናት።
ዌልስም ይህንን በመከተል በ2022 ሕግ አውጥታለች። ሆኖም በሰሜን አየርላንድ እና እንግሊዝ ቅጣቱ እስካሁን ሕጋዊ እንደሆነ ነው።
አንዳንዶች ክልከላው ወጣቶችን ከጥቃት ይጠብቃል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ወላጆችን ወንጀለኛ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ተቃውመውታል።
በሳልፎርድ የቤቢ ኮሌጅ ባለቤት የሆነችው ኤሚይ ውድስ ፣ ክልከላውን በእንግሊዝም ማየት እንደምትፈልግ ተናግራለች። " እስካሁን አለመኖሩንም ማመን አልቻልኩም" ብላለች።
"ሕፃናት ፍቅር እና ኃላፊነት የተሞላበት ግንኙነት እንዲሁም መጫዎት ይፈልጋሉ። በልጅነት እድሜያቸው ቅጣት ሊፈፀምባቸው አይገባም" ስትልም አክላለች።
የ10 ወር ልጅ እናት የሆነችው ሳራም አካላዊ ቅጣት ሕጋዊ መሆኑ እንዳስገረማት ገልጻለች።
በኬንት ዩኒቨርሲቲ በቤተሰብ እና ወላጆች አጥኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ሊ " ጥናቱ "አሳማኝ" ቢሆንም "ሙከራ ለማካሄድ እና ምክንያቶቹን ለመለየት የተቻኮለ ነው" ብለዋል።
ምክንያታቸውን ሲያስረዱም በሕፃናት እድገት የሚከሰቱ ብዙ ነገሮች ምክንያቶቹ ብዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አካላዊ ቅጣትን የሚደግፉት 'ቢ ሪዝነብል ኢንግላንድ' የሚለው ዘመቻ ተሳታፊ የሆኑት ሊ በበኩላቸው" ሕፃናት ጥሩ ስንሆንላቸው ጥሩ እንደሚሆኑ በማሰብ ለእነሱ መልካም ብንሆን አሪፍ ነው" ብለዋል።
ሆኖም ሕፃናት የማኅበረሰቡን ሕግ እንዲረዱ እና በዚያው መሠረት ሥርዓት እንዲይዙ ለማድረግ ገደብ ሊኖረን እና ገደቦች ሊበጁ ይገባል" ሲሉም አስረድተዋል።
የለንደን ኮሌጅ ዩኒቨርስቲ ጥናት በ2021 ከአምስት የ10 ዓመት ልጆች ውስጥ አንዱ በሆነ መልኩ አካላዊ ቅጣት የተፈፀመበት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ከፍተኛ ትምህርት የደረሱ እናቶች አካላዊ ቅጣትን የመጠቀማቸው እድል አነስተኛ መሆኑን አመልክቷል።
የሰሜን አየርላንድ አስተዳዳሪ በጥናቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።