የአፍሪካ እና የካሪቢያን አገራት በጥቁሮች ላይ ለተፈጸመው የባሪያ ንግድ ይፋዊ ይቅርታ እና ካሳ ጠየቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአፍሪካ እና የካሪቢያን አገራት አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ ከተካሄደው የባሪያ ንግድ የተጠቀሙ አገራት በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዲሁም ካሳ እንዲከፍሉ ጠየቁ።

የአፍሪካ እና ካሪቢያን አገራት መሪዎች በጋና ለሦስት ቀናት ያካሄዱትን ጉባዔ ሲያጠናቅቁ በባሪያ ንግድ ለተጎዱ አገራት ፍትሕ እንዲሰፍን ጠይቀዋል።

ያለፈው መጋቢት ላይ የተባበሩት መንግሥታት ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የባሪያ ንግድ "በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች የከፋው" መሆኑን ግልጿል። የተመድ አባል አገራት የካሳ ገንዘብ እንዲያዋጡም አሳስቧል።

ከ15ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያን ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ወደ አሜሪካ ግዛቶች በባርነት ተወስደዋል።

በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚለውን በተመለከተ በጋና መዲና አክራ በተካሄደው ጉባዔ ላይ 19 ነጥቦች ያሉት ዕቅድ ይፋ ተደርጓል።

ሁሉን አቀፍ የዕዳ ቅነሳ እንዲደረግ፣ የተዘረፉ ባህላዊ ንብረቶች እንዲመለሱ እና ዓለም አቀፍ የካሳ ማዕቀፍ እንዲዘረጋ ተጠይቋል።

ለዓለም አቀፍ የካሳ ማዕቀፉ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚሰጥ አልተጠቀሰም።

ቅኝ ግዛት በአፍሪካውያን ሴቶች እና ታዳጊዎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ተለይቶ እንዲታይም ተጠይቋል።

ቀድሞ በባሪያ ንግድ ውስጥ የተሳተፉ አገራት "ሙሉ፣ ይፋዊ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው ይቅርታ" መጠየቅ እንዳለባቸው የጉባዔው ተሳታፊዎች ተስማምተዋል።

የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሀማ "ታሪክ ጥፋተኛነትን እንድንወርስ አይጠይቀንም፤ ኃላፊነት መውሰድ ግን አለብን" ሲሉ ለአፍሪካውያን እና የካሪቢያን መሪዎች ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት የቅኝ ግዛት ሰለባዎች "ከሰው በታች፣ እንደ እቃ ተቆጥረዋል" ብለዋል።

ሆኖም ግን ካሳን ወደ ገንዘብ ብቻ ማውረድ እንደማይገባ ተናግረዋል። "ቼክ መጻፍ ብቻውን የታሪኩን ምዕራፍ አይዘጋም" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የውሳኔ ሐሳብ ያሳለፈው በ123 ድጋፍ፣ በ52 ድምጸ ተአቅቦ እና በሦስት ተቃውሞ ነው። የተቃወሙት አሜሪካ፣ እስራኤል እና አርጀንቲና ናቸው።

ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አብዛኞቹ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።

የተመድ የጠቅላላው ጉባዔ የውሳኔ ሐሳቦች እንደ ፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች በሕግ አሳሪ አይደሉም።

ዩናይትድ ኪንደግም (ዩኬ) ካሳን ከሚቃወሙ አገራት አንዷ ናት። ለቀድሞ ጥፋት አሁን ላይ ዋጋ መክፈል ተገቢ አይደለም ብላ ትከራከራለች።

በተመድ የዩኬ አምባሳደር ጄምስ ካሪውኪ "የትኛውም ሰብአዊ ቀውስ ከሌሎቹ በተለየ ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ ተደርጎ መወሰድ የለበትም" ብለዋል።

የአሜሪካ አምባሳደር በበኩላቸው አገራቸው "ቀድሞ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ሕገ ወጥ ላልነበረ ክስተት አሁን ላይ ካሳ በመክፈል" እንደማታምን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ካሳው ለእነማን እንሆነ በግልጽ እንዳላስቀመጠም ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ በቅኝ ግዛት ለተወሰዱ አፍሪካውያን ቤተሰቦች ወይም ጉዳት ለደረሰባቸው አፍሪካውያን ካሳ የከፈለ አገር የለም።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሰዎችን በባርነት ይዘው ለነበሩ ግለሰቦች በመንግሥታት አማካኝነት ካሳ ቢሰጥም ለተጎጂዎች ገንዘብ አልተከፈለም።

ቅኝ ግዛት ሕገ ወጥ ሲደረግ በአውሮፓውያኑ በ1830ዎቹ የዩኬ መንግሥት ሰዎችን በባርነት ለያዙ ዜጎቹ ከ21 ቢሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ ሰጥቷል።