አሜሪካ ፡ ባይደን በትራምፕ ስር የነበረውን ፕሬዝዳንታዊ የትዊተር ገጽን እንደማይወርሱ ተገለጸ

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
ታትሟል

ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባደን አዲሱ ይፋዊ ፕሬዚዳንታዊ የትዊተር ገጽ ያገኙ ሲሆን፤ ይህም ምንም አይነት ተከታይ የሌለው ከዜሮ ለመጀመር ተገደዋል።

ይህ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ሽግግር የተለየ በመሆኑ የባይደን ሰዎችን አሳዝኗል።

አዲሱ ትዊተር በተመራጩ ፕሬዝዳንት ስም የተከፈተው የትዊተር ገጽ ባይደን ከቀናት በኋላ በዓለ ሲመታቸውን ሲያከናውኑ ወደ ይፋዊው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በሚል ይቀየራል።

የፕሬዝዳንቱ አዲሱ የትዊተር ገጽ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ወደ 400 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮችን አፍርቷል።

ጆ ባይደን ቀደም ሲል ሲገለገሉበት የቆየው ግላዊ የትዊተር ገጻቸው ወደ 24 ሚሊዮን የሚደርሱ ተከታዮች አሉት።

የአዲሱ ፕሬዝዳንት ባይደን ቡድን ተጨማሪ አዳዲስ የትዊተር አካውንቶችንም አስመዝግበዋል ከእነዚህም ውስጥ ለፕሬዝዳንቱ ባለቤትና የወደፊቷ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ይገኝበታል።

ዶናልድ ትራምፕ ከኦባማ የወረሱት የትዊተር አካውንት 13 ሚሊዮን ያህል ተከታዮች የነበሩት ሲሆን፤ አሁን ግን ይህ የትዊተር አካውንት ዝውውር ተግባራዊ አልተደረገም።

ይህን የትዊተር እርምጃ ለባይደን ቡድን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተገለጸለ ሲሆን በዚህም "አዲሱ አስተዳደር ከዜሮ መጀመር አለበት" ማለት ነው።

ትዊተር እዚህ ውሳኔ ላይ ለምን እንደደረሰ አልገለጸም።

"አዲሱ አስተዳደር ተከታዮቹን ከቀድሞው አስተዳደር በቀጥታ አይወስድም" ብሏል ትዊተር ምክንያቱን ግልጽ ሳያደርግ።

ግን ቀደም ሲል ይፋዊውን የፕሬዝዳንቱን እና የምክትሉን ትዊተር የተከተሉ ሰዎች፣ የባይደንን እና የተመራጯን ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሃሪስን የግል ትዊተር የሚከተሉ ሰዎች አዲሱን የፕሬዝዳንት አካውንት መከተል እንዲችሉ ማሳወቂያዎችን ይደርሳቸዋል ተብሏል።

ኦባማ ኦፊሴላዊ የትዊተር አድራሻ ያላቸው የመጀመሪያው የአሜሪካ መሪ ነበሩ። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በሚል መለያ የተከፈተው አካውንት በ2015 ነበር የተከፈተው።

በሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ላይ ኦፊሴላዊን አካውንት ለትራምፕ ለማስረከብ የሽግግር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ አዲሱ አስተዳደር ተላልፎ ነበር።

ሁሉም የኦባማ ይፋዊ ትዊቶች በተለየ መለያ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ በሚል በመቀመጡ አሁን ድረስ ሊነበቡ ይችላሉ።

ትዊተር በይፋዊው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የትዊተር አካውንት ሥር ያሉ መረጃዎች ማግኘት እንደሚቻል አስታውቋል። ዶናልድ ትራምፕ የራሳቸውን የትዊተር ገጽ በማስቀደም ኦፊሴላዊውን የአገሪቱን ፕሬዝዳንት የትዊተር ገጽ ብዙም አይጠቀሙም።

ትዊተር ስለታገደው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አካውንት ምንም ያለው ነገር የለም። የያዛቸው መረጃዎች ለታሪክነት ስለመቀመጣቸው ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠትም ፈቃደኛ አልሆነም።