"የትራምፕ ከትዊተር መታገድ ትክክለኛ ቢሆንም አደገኛ ነው" የትዊተር ኃላፊ

የትዊተር ስራ አስፈፃሚ ጃክ ዶርሴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአወዛጋቢ መልዕክቶቻቸው ከትዊተር እንዲታገዱ የተደረጉትን የአሜሪካ ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እግድ አስመልክቶ ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ የትዊተር ኃላፊ ጃክ ዶርሴይ ተናግሯል።

ነገር ግን ሁኔታው እንዳሳዛነው ያልደበቀው ኃላፊው "ያልተለመደና መቀልበስ የማይችል" ድርጊት ተከስቷል" በማለትም የትራምፕን እግድ የገለፀው።

ኃላፊው አክሎም በተወሰነ መልኩ ጥፋቱ የትዊተር እንደሆነና "ጤናማ የሆኑ ንግግሮችንና ውይይቶች" እንዲዳብሩ ለማድረግ በቂ ስራ አልሰራም ብሏል ድርጅቱ።

የትራምፕ የትዊተር ገፅ መታገድ ተከትሎ የተቀላቀሉ ስሜቶችን አስተናግዷል። አንዳንዶች ውሳኔውን ሲያሞግሱት ሌሎች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ተችተውታል።

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርኬልና የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር ምንም እንኳን የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ወዳጆች ባይሆኑም የትዊተር ውሳኔን ከተቹት መካከል ይገኙበታል።

የካፒቶሉን አመፅ ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ከትዊተር እንዲታገዱ ውሳኔ ቢያሳልፍም ኃላፊው ደስታም ሆነ ኩራት እንዳልተሰማው በትዊተር ገፁ አስተላልፋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ ግልፅ ማስጠንቀቂያ ከተላለፈላቸው በኋላም እንደታገዱ አስታውቋል።

"ውሳኔውን ስንወስን በኢንተርኔት እንዲሁም ከኢንተርኔት ውጭ ባለው የአካላዊ ደህንነት ስጋት እንደሚጋርጥ በማመን ነው" ብሏል ጃክ ዶርሲ

ሆኖም ይህ ውሳኔ ለነፃና ክፍት ኢንተርኔትም መሰናክል ሊሆን እንደሚችልም አምኗል።

"እንዲህ አይነት ውሳኔዎችን መወሰን የማህበረሰቡን እይታ ይከፋፍሉታል። እንደ ህዝብም ይከፋፍሉናል እናም አደገኛ እንደሆነ ይሰማኛል" ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በኢንተርኔት ላይ ድምፃቸውን ማሰማት የሚችሉትንም ሆነ ሳንሱር ማድረግ የጥቂት ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ኃላፊነት ሆኗል በማለት ለተቹትም ምላሽ ሰጥቷል።

"ኩባንያዎች ሁኔታውን ለመቆጣጠር የቢዝነስ ውሳኔ መወሰን መንግሥት ከሚያደርገው ክልከላ ጋር ይለያያል። ሆኖም ተመሳሳይ ስሜት አለው" ብሏል ጃክ

የትዊተር ተጠቃሚዎችን ማገድ፣ ፅሁፋቸውን ማጥፋትና ሌሎች በትዊተር የሚደረጉ ውሳኔዎች ነፃ እሳቤንና ንግግርን ይጥሳሉ በማለትም ትችት ቀርቦበታል።