የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩቲዩብ ገጽ ታገደ

የፎቶው ባለመብት, Google/Getty Images
ከታዋቂዎቹ የማልበራዊ ትስስር መድረኮች መካከል አንዱ የሆነው ዩቲዩብ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የድርጅቴን ደንብ ጥሰዋል በሚል አግዷቸዋል።
በጉግል ባለቤትነት የሚተዳደረው ዩቲዩብ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አዳዲስ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዳይለጥፉ ወይንም ደግሞ በቀጥታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዳያጋሩ ለሰባት ቀን ያህል ማገዱን ያስታወቀ ሲሆን፤ እግዱ ከዚህም ረዘም ያለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
ኩባንያው የዶናልድ ትራምፕን ገጽ፣ የድርጅቱን አመጽን አለማነሳሳት የሚለውን ደንብ ጥሷል ሲል ተናግሯል።
ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ማታ በርካታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ያጋሩ ሲሆን የተወሰኑት አሁንም በሰሌዳቸው ላይ ይገኛሉ።
ዩትዩብ ባገዳቸው የዶናልድ ትራምፕ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ውስጥ ምን እንዳሉ የጠቀሰው ነገር የለም።
ይህ ውሳኔ የተሰማው የተለያዩ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ፕሬዝዳንቱ ከዩቲዩብ እንዲታገዱ የሚጠይቅ ማስታወቂያ ለመልቀቅ ከዛቱ በኋላ ነው።

የፎቶው ባለመብት, YouTube
ከዚህ በፊት ፕሬዝዳንቱ ከፌስቡክ እንዲታገዱ ሲቀሰቅስ የነበረው ጂም ስቴየር ዩቲዩብ የፕሬዝዳንቱን ቻናል እስከመጨረሻው በመዝጋት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
"እስከወዲያኛው ይዘጉታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለትራምፕ እዚህ መድረስ ግጭትን መቀስቀሱ በጣም አሳዛኝ ነው፣ ነገር ግን ዋነኛ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል" በማለት ከእገዳው በኋላ በትዊተር ሰሌዳው ላይ ለጥፏል።
ጉግል እንዳለው ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ ገጻቸው ከዚህ የድርጅቱን ፖሊሲ የሚቃረን ጥፋት ሰርተው ከተገኙ እስከ መጨረሻው የሚታገዱበት እድል አለ።
ዶናልድ ትራምፕ አመጽን በማነሳሳት ይህ የመጀመሪያ ጥፋት ሆኖ የተመዘገበባቸው ሲሆን፣ ዳግመኛ ተመሳሳይ ሁለት ጥፋቶች ከተመዘገበባቸው እስከ ወዲያኛው ከገጹ ላይ ይሰናበታሉ ብሏል ድርጅቱ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በካፒቶል ሂል የነበረውን አመጽ ተከትሎ ቢያንስ ጆ ባይደን ስልጣን እስኪረከቡ ድረስ ከፌስቡክ እና ከኢንስታግራም ታግደዋል።
ትዊተር በበኩሉ በቋሚነት የፕሬዝዳነቱን አካውንት አግዶታል።
አማዞን ትዊች ገጻቸውን እንዳይሰራ ያደረገ ሲሆን ስናፕቻት በበኩሉ ዘግቶባቸዋል።
ሾፒፋይ፣ ፒንትረስት፣ ቲክቶክ እና ሬዲት ፕሬዝዳንቱ ለተከታዮቻቸው የሚያጋሩትን ላይ ገደብ ጥለዋል።

















