እንግሊዛዊቷ ተዋናይት 208 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር ተከሰሰች

ኤማ ሑሴን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኤማ ሑሴን የተባለችው እንግሊዛዊት ተዋናይ በምዕራብ አፍሪካ በኩል 320 ኪሎግራም የሚመዝን አደንዛዥ ዕፅ ወደ አውስትራሊያ ልታስገባ በመሞከሯ ተከሰሰች።

የ34 ዓመቷ ተዋናይት ሜት የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ለማዘዋወር በመሞከር ክስ ሲድኒ የሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርባለች። በዚህ ክስ ከፍተኛው ፍርድ የዕድሜ ልክ እስራት ነው።

ተዋናይቷ ደቡብ አውስትራሊያ ከሚኖሩ ጥንዶች ጋር በመመሳጠር አደንዛዥ ዕፁን በከሰል ጆንያ ውስጥ ደብቀው ለማሳለፍ መሞከራቸውን ፖሊስ ገልጿል።

የከሰል ጆንያዎቹ የተጫኑት ከጋና ሲሆን አደንዛዥ ዕፁ 208 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል።

ፍርድ ቤት የተዋናይቷን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

በአውሮፓውያኑ 2013 በተለቀቀው 'ሀሚንግበርድ' ፊልም ላይ በመተወን የምትታወቀው ኤማ፤ መከሰሷን ተከትሎ የአውስትራሊያ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ፤ ከጋና ተነስተው ሲድኒ የባሕር ዳርቻ ባረፉ መርከቦች ላይ በተደረገ ፍተሻ አደንዛዥ ዕፁ መያዙን አስታውቋል።

አደንዛዥ ዕፁን በከሰል ጆንያ ውስጥ ደብቀው ለማሳለፍ ሞክረዋል

የፎቶው ባለመብት, Australian Federal Police/Australian Border Force

የምስሉ መግለጫ, አደንዛዥ ዕፁን በከሰል ጆንያ ውስጥ ደብቀው ለማሳለፍ ሞክረዋል

ፖሊስ አደንዛዥ ዕፁን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ተዋናይቷ በመርከብ ላይ የተጫነውን የከሰል ጆንያ ብዙ ሰዎች እንዲያወርዱ እና በመኪና እንዲጭኑ ለማስተባበር መሞከሯን ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ በከፈተውምርመራ የ30 ዓመት ሴት እና የ32 ዓመት ወንድን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ ባልደረባ ትሬቨር ሮቢንሰን "ገበያው ላይ ወደ 296 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ የሚችል አደንዛዥ ዕፅ ነው" ብለዋል።

"የወንጀል ቡድኖች አደንዛዥ ዕፅን ደብቀው ለማስገባት ብዙ ሙከራዎች ያደርጋሉ። በከሰል ውስጥ መደበቅ አንደኛው መንገድ ቢሆንም ባልደረቦቻችን ደርሰውበታል" ብለዋል።

ተዋናይቷ በቁጥጥር ሥር ስትውል ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች እና ማስታወሻ ደብተር ይዛ ነበር።