በዩክሬን ጥቃት ሳቢያ 'ጥቁር ዝናብ' እየጣለ መሆኑን የሞስኮ ነዋሪዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ጥቁር ጋዝ የቀላለቀ ዝናብ እየጣለ እንደሆነ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ዩክሬን በሞስኮ ላይ ካደረሰቻቸው ጥቃቶች የከፋው ሲሆን፤ ዩክሬን ወደ ሩሲያ መዲና ወደ 200 የሚጠጉ ድሮኖችን ተኩሳለች።
የሞስኮ ሰማይ በጥቁር ጭስ እንደታፈነ እና 17 ሰዎች እንደተጎዱ አገረ ገዢው አንድሪ ቮሮብዮቭ ተናግረዋል።
በደቡብ ምሥራቅ ሞስኮ የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት ዝናቡ ልብሳቸው ላይ "አስቀያሚ" ጥቁር ምልክት ይጥላል።
የሞስኮ ባለሥልጣናት "ጋዝ የቀላቀለ ዝናብ" መውረዱን ቢያስተባብሉም፤ በቴሌግራም ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ነዋሪዎች መስኮታቸውን እንዲዘጉ እና አስም ያለባቸው ሕጻናት እና አረጋውያን አካባቢው ለቅቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ባለፉት 24 ሰዓታት ወደ 1,000 የሚጠጉ የዩክሬን ድሮኖችን ማምከን ተችሏል።
በሞስኮ ደቡባዊ ግዛት በምትገኘው ሮስቶቭ የነዳጅ ፋብሪካ ላይ በደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ተገድሏል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንዳሉት የድሮን ጥቃቱ ባለፈው ሳምንት ሩሲያ በቪቭ ላደረሰችው ድብደባ የአጸፋ ምላሽ ነው።
ሩሲያ ባለፈው ሳምንት በኪቭ በሚገኘው ፔቼራስክ ገዳም አካባቢ ጥቃት ማድረሷን ጠቅሰው "እኛ ጦርነቱን አንፈልገውም፤ አልፈለግነውምም። ዩክሬን ከተቃጠለች ግን ሞስኮም ትነዳለች" ሲሉ ዝተዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ "ቃላት ብቻ በቂ አይደሉም። ዩክሬን መጠነ ሰፊ ዋጋ ትከፍላለች" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በሞስኮ የሚገኘው ካፖታንያ ነዳጅ ፋብሪካ በአንድ ወር ውስጥ ሦስት ጊዜ ጥቃት ተፈጽሞበታል። አካባቢው በጥቁር ጭስ ታፍኖ የሚያሳዩ ቪድዮዎችም ወጥተዋል።
የድሮን ስብርባሪ በመውደቁ ምክንያት በአቅራቢያው በሚገኝ መደብር እሳት መነሳቱ ተገልጿል።
ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ባረጋገጠው ቪድዮ ላይ በአንድ ሕንጻ አናት ላይ ድሮን ሲወድቅ ይታያል።
በሌላ በተረጋገጠ ቪድዮ ላይ ደግሞ ጥቁር እና በጋዝ የተሞላ ፍንጥቅጣቂ መኪና ማቆሚያ ላይ ሲወርድ መመልከት ይቻላል።
አንድ ነዋሪ "ከቤቴ ስወጣ እያካፋ ነበር። ልብሴ ላይ ደስ የማይል ጥቁር ነጠብጣብ ጥሎብኛል። ፔትሮሊየም የሚፈስ ከሆነ ፀጉራችን ተነቃቅሎ እስከሚወድቅ ልንጠብቅ ነው ማለት ነው" ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።
የሩሲያ ባለሥልጣናት የድሮን ጥቃቱ ያደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምሥሎች እና ቪድዮዎች ማጋራትን ቢከለክሉም በርካታ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እየወጡ ነው።















