በዶናልድ ትራምፕ ምክንያት በርካቶች የሚበሉትና የሚኖሩበትን ሊያጡ ይችላሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበላቸውን የኮቪድ-19 ድጎማን ባለመፈረማቸው ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ጥቅማ ጥቅም ማግኘት አልቻሉም።
ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፤ ትራምፕ ፊርማቸውን የማያሳርፉ ከሆነ "መዘዙ የከፋ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
በዚህም ሳቢያ በርካታ ሚሊዮን ሥራ አጥ አሜሪካዊያን ያለምንም ጥቅማ ጥቅም የቀሩ ሲሆን፤ የቤት ኪራይ መክፈል የማይችሉ አሜሪካዊያን ደግሞ ቤት አልባ ሊሆኑ ይችላሉ።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ኮንግረስ አቅም ለሌላቸው አሜሪካዊያን በነብስ ወከፍ 600 ዶላር እንዲሰጥ የሚያዝ ድጎማ ለትራምፕ ቢያቀርቡም ፕሬዝደንቱ ገንዘቡ አንሷል ብለዋል ተቃውመውታል።
አሜሪካዊያን ፖለቲከኞች ለወራት በድጎማው ጉዳዩ ከተከራከሩ በኋላ የ900 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አፅድቀዋል።
ትራምፕ አሜሪካዊያን በነፍስወከፍ የሚገባቸው 600 ዶላር ሳይሆን 2 ሺህ ዶላር ነው ይላሉ።
ነገር ግን ኮንግረስ ውስጥ ያሉ የትራምፕ ፓርቲ አባል የሆኑ ሪፐብሊካኖች ግን ይህን አልተቀበሉትም።
በአሜሪካ የሰዓት አቆጣጠር ቅዳሜ አመሻሹን ፕሬዝደንቱ አሁንም አቋማቸውን እንዳልቀየሩ በትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።
"ይህ የአሜሪካዊያን ችግር አይደለም፤ የቻይና እንጂ። ሁለት ሺህ ዶላር እንደውም ሲያንስ ነው" የሚል መልዕክት ያለው ፅሑፍ አስፍረዋል።
ኮንግረሱ ያፀደቀው ድጎማ 1.4 ትሪሊዮን ዶላር የፌዴራል መንግሥት በጀትንም የያዘ ነው።
ትራምፕ ፊርማቸውን ካላሳረፉ አሊያም ኮንግረሱ በእሳቸው ሐሳብ ካልተስማማ ከማክሰኞ ጀምሮ የአሜሪካ መንግሥት መስሪያ ቤቶች በከፊል መዘጋት ይጀምራሉ።
14 ሚሊዮን ገደማ ሥራ የሌላቸው አሜሪካዊያን በዚህ ሳቢይ ክፉኛ ሊጎዱ እንደሚችሉ ተገምቷል።
ባይደን ምን አሉ?
ጠንከር ያሉ ቃላት ያዘለ መግለጫ ያወጡት ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትራምፕ ፊርማቸውን ማኖር አለማቻላቸው "ኃላፊነትን አለመወጣት" ነው ብለዋል።
"ቀኑ የገና ማግስት ነው። ነገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ፕሬዝደንት ትራምፕ ድጎማውን አላፀድቅም በማለታቸው ምክንያት በልተው መዋላቸውን እንኳ እርግጠኛ መሆን አልቻሉም" ብለዋል ባይደን።
የአሜሪካ ኮንግረስ የኮሮናቫይረስ ድጎማውን በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁን ያደነቁት ባይደን "ትራምፕም ይህን በማድረግ በዚህ የበዓል ሰሞን አሜሪካዊያን ጠረጴዛቸው ላይ ምግብ ማስቀመጥ እንዲችሉና አረፍ የሚሉበት ቤት እንዲኖራቸው ሊያደርጉ ይገባል" ብለዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው "እኔ፤ ታላቁ የአሜሪካ ሕዝብ 600 ዶላር ሳይሆን 2 ሺህ ዶላር እንዲያገኝ ነው የምፈልገው" በማለት በሐሳባቸው ፀንተዋል።
የኮሮናቫይረስ ድጎማና ሌሎችም በርካታ በጀቶች የተካተቱበት የገንዘብ ማዕቀፍ ወደ አሜሪካ ኮንግረስ ቀርቦ በአብላጫ ድምፅ ቢፀድቅም ትራምፕ ይህ "ውርደት" ነው ሲሉ ገልፀውታል።
አልፎም ማዕቀፉ "በአላስላፈጊ በጀቶች የተሞላ ነው" ሲሉ ትራምፕ አጣጥለውታል።
በማዕቀፉ ውስጥ የተካተቱ ለሌሎች አገራትም እንዲሰጡ የታቀዱ ድጋፎችን የተቃወሙት ትራምፕ "ይህ ገንዘብ ለአሜሪካዊያን ነው ሊሆን የሚገባው" የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።
የትራምፕ ሐሳብ በርካታ ፖለቲከኞችን አስደንቋል፤ አስደንግጧል።
ተንታኞች ፕሬዝደንቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት አቅማቸው ለደከመ አሜሪካዊያን እንዲሆን ድጎማ ይሰጥ ተብሎ ክርክር ሲደረግ አንዳችም ሐሳብ አላነሱም፤ አሁን ደርሰው ይህን ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።
የዶናልድ ትራምፕ አጋር የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትሩ ስቲቨን መንቺን 600 ዶላሩን ደግፈው ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስተያየት ሲሰጡ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን ድረስ ቆይተው ይህን ማለታቸው ለምን ይሆን? እያሉ በርካቶች እየጠየቁ ነው።
















