እግር ኳስ ፡ የዲያጎ ማራዶና የአስከሬን ምርመራ ውጤት ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአንድ ወር በፊት በልብ ችግር ምክንያት ያረፈው የቀድሞው የዓለም የእግር ኳስ ኮከብ በዲያጎ አርማንዶ ማራዶና አስከሬን ላይ የተደረገው ምርምራ ይፋ ሆነ።
የአርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ የአስከሬን ምርመራ እንዳረጋገጠው ህይወቱ ባለፈበት ጊዜ ምንም አይነት አልኮልም ሆነ ዕጽ መውሰዱን የሚያሳይ ምልክቶች እንዳልተገኙ ተገልጿል።
በአውሮፓውያኑ 1986 ላይ በተደረገው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ላይ ኮከብ በመሆን አገሩ አርጀንቲና በአሸናፊነት ዋንጫ እንድትነሳ ያስቻለው ማራዶና በኅዳር ወር ላይ ነበር በድንገት ህይወቱ ያለፈው።
ማራዶና በሞተበት ጊዜ ለህይወቱ ማለፍ በርካታ መላምቶች ሲቀርቡ የነበረ ሲሆን፤ በአስከሬኑ ላይ በተደረገው ምርመራ ተገኘው ውጤት ግን ከብዙዎች ግምት የተለየ ሆኗል።
ምርመራው እንዳመለከው የ60 ዓመቱ ማራዶና በኩላሊቱ፣ በልቡ ላይና በሳምባው ላይ ችግሮች ነበሩበት ተብሏል።
በእግር ኳስ ኮከቡ አስከሬን ላይ ምርመራ እንዲደረግ የታዘዘው በተለይ ማራዶና ህይወቱ ከማለፉ በፊት በተደረገለት የህክምና ድጋፍ ዙሪያ ለሞቱ ምክንያት ሊሆን የሚችል ማንኛውም አይነት ቸልተኝነት ከነበረ ለማጣራት ነበር።
የምን ጊዜም የእግር ኳስ ኮከብ ተደርጎ የሚታሰበው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ በአንጎሉ ውስጥ ላጋጠመው የደም መርጋት የተሳካ የቀዶ ህክምና ተደርጎለት የነበረ ሲሆን፤ በተጨማሪም ለነበረበት የአልኮል ሱስ ህክምና ለመጀመር እየተዘጋጀ ነበር።
ከአገሩ አርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ባሻገር ለቦካ ጁኒየርስና ለናፖሊ ክለቦች የተጫወተው ማራዶና ህይወቱ ባለፈበት ዕለት በአስከሬኑ ላይ ምርመራ በተደረገበት ጊዜ በከባድ የልብ ችግር ምክንያት መሞቱን ለመወቅ ተችሎ ነበር።
ከማራዶና ሞት ጋር በተያያዘ በመጨረሻው ሰዓት የህክምና ድጋፍ ያደረገለት ዶክተር ህይወቱን ለማዳን ተገቢውን ድጋፍ አላደረገም በሚሉና በሌሎችም ጉዳዮች ሲወቀስ የቆየ ቢሆንም በመጨረሻ የተገኘው የአስከሬን ምርመራ ውጤት ግን ነጻ ያወጣዋል ተብሏል።
ከማራዶና ሞት በኋላ የሦስት ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት በመላዋ አርጀንቲና ታውጆ አስከሬኑ በዋና ከተማዋ ቦነስ አይስ ውስጥ በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተቀምጦ፤ አገሬው በከፍተኛ ቁጥር በመገኘት ሐዘኑን በመግለጽ እንደተሰናበተው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የማራዶና አስከሬን እስካሁን እንደተቀመጠ ይገኛል ለዚህም ምክንያቱ ከተደረገው ምርመራ ባሻገር ከማራዶና ሞት በኋላ ኮከቡን የእግር ኳስ ተጫዋች አባትነት የሚጠይቅ አቤቱታ ለፍርድ ቤት በመቅረቡ ነው።
ለዚህም የአርጀንቲና አንድ ፍርድ ቤት የማራዶና አስከሬን ለዘረ መል (DNA) ምርመራ ስለሚፈለግ "ባለበት ይጠበቅ" የሚል በሰጠው ውሳኔ መሰረት አስከሬኑ ለጊዜው ቦነስ አይረስ ውስጥ በሚገኝ አንድ የግል የአስከሬን ማቆያ ውስጥ እንዲቆይ ተወስኗል።















