ትራምፕ የፌዴራል መንግሥት ሕንጻዎች "ቆንጆ" እንዲሆኑ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ

ትራምፕ ከዚህ በኋላ የሚገነቡ የፌዴራል መንግሥት ሕንጻዎች "ቆንጆ" እንዲሆኑ ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የስልጣን ዘመናቸው እየተገባደደ የሚገኘው አወዛጋቢው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አንድ ያልተለመደ ፍጹማዊ የአስተዳደር ውሳኔን አስተላልፈዋል።

ትዕዛዙ ከዚህ በኋላ የሚገነቡ ማናቸውም የፌዴራል መሥሪያ ቤት ሕንጻዎች "ቆንጆ" ብቻ ሆነው እንዲሰሩ ይላል።

በተለይም ዲዛይናቸው የብሉይ ግሪክ፣ ሮማዊያንና እንደዚያ የመሰለ ጥንታዊ ግርማን የተላበሰ እንዲሆን ፕሬዝዳንቱ ቀጭን ትእዛዝ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፉት አሁን ያሉ የፌዴራል ቢሮ ሕንጻዎች የቀድሞውን "ክፉ" ጊዜና ሥርዓት የሚያስታውስ ነገር አላቸው በሚል ነው።

ሆኖም መሆን የነበረበት የአሜሪካ ሕንጻዎች መንፈሳቸው ደስ የሚያሰኝ፣ ተወዳጅና ዐይነ ግቡ እንጂ ሌላ አልነበረም ብለዋል።

ብዙዎቹ የመንግሥት ሕንጻዎች ውብ ኪነ ሕንጻ መልክን የተላበሱ መሆን ሲገባቸው ቀፋፊ መልክን ይዘዋል ብለዋል ትራምፕ።

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በኋላ የሚሰራ ማንኛውም የፌዴራል ሕንጻ ልክ እንደ ዋይት ሐውስ ቀልብን የሚገዛ እንዲሆን እፈልጋለው ብለዋል።

በርካታ የኪነ ሕንጻ ነገር ግድ የሚላቸው አሜሪካዊያን ሐሳቡን የደገፉ ሲሆን ቅሬታ የገባቸውም ግን አልጠፉም።

የአሜሪካ የኪነ ሕንጻ ኢንስቲትዩት የትራምፕን ሐሳብ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሲል ተቃውሞታል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ፍጹማዊ የአስተዳደር ደንብ "Promoting Beautiful Federal Civic Architecture" የሚል ደንብ ሆኖ ተመዝግቧል።

ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት አልሚ የነበሩ በመሆናቸው ለሚሰሩ ፎቆች ጥራትና ሥነ ሕንጻ ውበት ግድ የሚላቸው ናቸው ይሏቸዋል።

ትራምፕ በቅርብ ጊዜ በዋሺንግተን ዲሲ የተገነቡ የፌዴራል ሕንጻዎች የብሉይና የዘመናይ ኪነ ሕንጻ ሽብልቆች በመሆናቸው አልወደዷቸውም።

በዚህም የተነሳ አንዳንድ የተጀመሩ የመንግሥት ሕንጻዎችን እስከማስቆም ደርሰዋል።

ቀደምት ማንነታችንን የሚያንጸባርቁ ጥንታዊነትን የተላበሱ ኪነ ሕንጻዎች ከዚህ በኋላ በሚገነቡ ፎቆች ዲዛይን ላይ አሻራ እንዲኖራቸው የትራምፕ ፍጹማዊ የአስተዳደር ደንቡ ያዛል።

የኪነ ሕንጻ ማኅበራት ግን እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚመርጠው የራሱ ኪነ ሕንጻ አሰራር እንጂ ይህን ገንባ ተብሎ ሊጫንበት አይገባም ሲሉ ፕሬዝዳንቱን ተቃውመዋል።