የኮሮናቫይረስ 'ቢያንስ እስከ አመቱ መጨረሻ ይቆያል'- የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቫይረሱ ቢያንስ እስከ መጪው የአውሮፓ በጋ ወቅት- ሰኔ ወር ይቆያል አሉ።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ የኮሮናቫይረስን የመዘገበችው አገራቸው ቫይረሱን ለመግታትም ትታገላለች ብለዋል።
ፓሪስ አካባቢ በሚገኝ ሆስፒታል ጉብኝታቸውን እያደረጉ የነበሩት ፕሬዚዳንት ቫይረሱ ቢያንስ እስከ መጪው የአውሮፖ በጋ ወቅት (ከሰኔ-ነሐሴ ወር) እንደሚቆይ ሳይንቲስቶችን ዋቢ በማድረግ ተናግረዋል።
ሆኖም አገራቸው ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ እግድ ወይስ በግማሽ ትጥላለች የሚለውን ለማወቅ ጊዜው ገና ነው ብለዋል።
በአገሪቷ 2/3ኛውን የሚሸፍነውና- 46 ሚሊዮን ህዝቦች ይኖሩባቸዋል በተባሉ ከተሞች ላይ የምሽት ሰዓት እላፊ ታውጇል።
በዚህ ሳምንት አርብ በፈረንሳይ 40 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 298 ዜጎቿንም አጥታለች።
በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን ሩሲያ፣ ፖላንድ፣ ጣልያን፣ ስዊዘርላንድም እንዲሁ ወረርሽኙ አገርሽቷል፤ ከፍተኛ ቁጥርም መዝግበዋል።
በአውሮፓ የታየውን የቁጥር ማሻቀብ በተመለከተም የአለም ጤና ድርጅት ቫይረሱን ለመግታት ቁልፍ ጊዜ ነው ብሏል።
የጤና ማዕከላትም በህመምተኞች ቁጥር እንዳይጨናነቁ አስቸኳይ ስራ ያስፈልጋልም ተብሏል።
በባለፉት አስር ቀናት በአውሮፓ በኮሮናቫይረስ በየቀኑ የሚመዘገበው ቁጥርም በእጥፍ ጨምሯል ተብሏል።
አህጉሪቷ እስካሁን ባለውም 7.8 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሲሆን 247 ሺህ ሰዎችንም በሞት ተነጥቃለች።
"የሚቀጥሉት ወራቶች ፈታኝ ነው የሚሆኑት፤ አንዳንድ አገራት ደግሞ በአደገኛ መንገድ ላይ ናቸው" በማለት የአለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 42 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ሟቾችም 1.1 ሚሊዮን ሆኗል።
ሳይንቲስቶች ክትባቱን ለማምረት ቀን ተሌት እየሰሩ ሲሆን አመርቂ ውጤቶች መታየታቸውም ተነግሯል።
ሆኖም ህይወት እንደቀደመው በቅርቡ አይመለስም፤ ክትባቱንም ለህዝቡ ለማዳረስ አንድ አመት ያስፈልጋልም እያሉ ነው።












