ፖላንድ፡ የጽንስ ማቋረጥ ሕግ መቀየሩን የተቃወሙ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሺዎች የሚቆጠሩ ፖላንዳውያን ሴቶች አዲሱን የጽንስ ማቋረጥ ሕግ በመቃወም በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሰልፍ ወጥተዋል።
ሐሙስ እለት የነበረ ችሎት ማንኛውንም የጽንስ ማቋረጥን ያገደ ሲሆን፣ በመደፈር፣ ዘመድ በሆኑ ግለሰቦች መካከል በተፈፀመ ግንኙነት ወይንም የእናቲቱ ጤና አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ ብቻ ይፈቀዳል ሲል አጽድቋል።
በፓላንድ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ጽንስ ለማቋረጥ እንደ ምክንያትነት ይጠቀሙት የነበረው እና ጽንሱ የጤና ችግር ካለበት ሊቋረጥ ይችላል የሚለው ሕግ አሁን ክልከላ ተደርጎበታል።
ከአውሮፓ ሕብረት አባላት መካከከል ፖላንድ ጥብቅ የጽንስ ማቋረጥ ሕግ ካላቸው አገራት መካከል ናት።
በአገሪቱ ከ2000 ያነሰ ሕጋዊ የጽንስ ማቋረጥ በየዓመቱ ይካሄዳል። ነገር ግን 200,000 ያህል የጽንስ ማቋረጦች ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ አልያም ከፖላንድ ውጪ ባሉ አገራት የሚፈፀሙ መሆናቸውን በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ይናገራሉ።
የተቃውሞ ሰልፎቹ በፓላንድ ትልልቅ ከተሞች መካሄዳቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
በፖላንድ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከ10 ሰው በላይ መሰብሰብ የተከለከለ ቢሆንም ለሁለተኛ ቀን ሰልፉ ቀጥሏል።
አርብ እለት ማለዳ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በዋርሶው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ አካባቢ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ነበር።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን በበላይነት የሚያስተዳድረው ፒአይኤስ ፓርቲ የሕግና ፍትህ የበላይ ኃላፊ ናቸው።
ፖሊስ፣ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ድንጋይ ቢወረውሩም እነርሱ ግን ኃይል መጠቀምን አለመፈለጋቸውን ገልጿል።
ሰልፈኞቹ አርብ ምሽት በድጋሜ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት አቅራብያ የተሰበሰቡ ሲሆን ፖሊስ ግን አሁንም ወደ ቤቱ እንዳይጠጉ ተከላክሏል።
ሰልፈኞቹ "ይህ ጦርነት ነው" እና "በእጅህ ላይ ደም አለ" የሚሉ መፈክሮችን ይዘው እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
በሌላ ከተሞች ግን ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በአደባባዮች፣ በአብያተ ክርስትያናት አካባቢ እና በፒአይኤስ ፖለቲካ ፓርቲ ሕንጻዎች አካባቢ ተሰባስበዋል።
የ34 ዓመቷ ማግዳ ከተቃዋሚ ሰልፈኞቹ መካከል አንዷ ስትሆን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን በሰጠችው ቃል ላይ "በዚህ አገር ሴቶች አይከበሩም። ማንም የሚያደምጠን የለም" ብላለች።
የፖላንድ የሴቶችና የቤተሰብ ምጣኔ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ክሪስቲና ካክፑራ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ስትናገር " የአገሪቱ ግማሽ ሕዝቦች ሴቶች ለሆኑባት ፖላንድ ውርደት ነው፤ በጭራሽ አንረሳውም" ብላለች።
ሐሙስ እለት የአገሪቱን የጽንስ ማቋረጥ ሕግ ያሻሻለው የአገሪቱ ሕገመንግስት ፍርድ ቤት "የጤና እክል ያለበትን" ጽንስን ማቋረጥ ከአገሪቱ ሕገመንግሥት ጋር አይሄድም ሲል ገልጿል።
ይህ ሕግ የማሻሻል ሃሳቡ የመጣው አገሪቷን ከሚያስተዳድረው ፒአይኤስ ፓርቲ ሲሆን አብዛኞቹ የፍርድ ቤቱ ዳኞችም በዚሁ ፓርቲ የተመረጡ ናቸው ተብሏል።
የዚህ አዋጅ መሻሻል በበርካታ የመብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቃውሞ ቢገጥመውም የአገሪቱ የሃይማኖት አባቶች ግን አወድሰውታል።












