ኮሮናቫይረስ፡ የፖላንዱ ፕሬዝዳንት በኮቪድ-19 ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድሬ ዱዳ በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ።
የፕሬዝዳንቱ ጤና ሁኔታ "መልካም" መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ራሳቸውን ለይተው ውሸባ ገብተዋል ተብሏል።
የ48 ዓመቱ ጉልማሳ ፕሬዝዳንት ዱዳ፣ አርብ እለት የኮሮናቫይረስ ማድረጋቸውንና መያዛቸው መታወቁ ዛሬ፣ ቅዳሜ ይፋ ተደርጓል።
ፕሬዝዳንቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ የተለያዩ ርዕሰ ብሄሮችን ያገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ይገኙበታል።
38 ሚሊዮን ዜጎች ያላት ፓላንድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት እያገረሸ ሲሆን አርብ ዕለት ብቻ ከ13 ሺህ 600 በላይ ሰዎች እንደሚያዙ የሚወጣው ሪፖርት ያሳያል።
አገሪቱ በአጠቃላይ " አደገኛ ቀጠና" ውስጥ መግባቷ የተገለፀ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና ሆቴሎች በከፊል ተዘግተዋል።
ፕሬዝዳንት ዱዳ በቫይረሱ እንዴት እንደተያዙ የተገለፀ ነገር ባይኖርም፣ ሰኞ ዕለት የቡልጋርያ ፕሬዝዳንት ሩመን ራዴቭ በተገኙበት በታሊን በተዘጋጀ በዓል ላይ ተገኝተው ነበር ተብሏል።
የቡልጋርያው ፕሬዝዳንት ከዚህ በዓል በኋላ ራሳቸውን ለይተው መቀመጣቸውን ተሰምቷል።
"ፕሬዝዳንቱ ትናንት ተመርምረው በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል" ሲሉ የፕሬዝዳንታዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው የትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
አክለውም የፕሬዝዳንቱን ጤንነት ለመከታተል ከአስፈላጊ ሕክምና ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ።
አውሮፓ እስካሁን ድረስ 7.8 ሚሊዮን በቫይረሱ ሲያዙ፣ በዚሁ ምክንያት ደግሞ 247 000 ሰዎች ሞተዋል።
በአውሮፓ ጣልያን፣ ኦስትርያ፣ ክሮሺያ፣ ስሎቫንያ እና ቦሲኒያ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጎዱ አገራት መካከል ናቸው።














