ቬትናም ፡ በመሬት ይዞታ ሰበብ ፖሊሶችን የገደሉ ቬትናማዊያን ሞት ተፈረደባቸው

በመሬት ይዞ ታ ሰበብ ቬትናም ውስጥ በተከሰተ ግጭት ለፖሊሶች ሞት ምክንያት ሆነዋል ከተባሉ 29 ሰዎች መካከል ሁለቱ የሞት ቅጣት ተፈረደባቸው።
የተቀሩት ተከሳሾች ደግሞ ከዕድሜ ልክ እስራት በገደብ እስከሚቆይ የ15 ዓመት እስር እንደተፈረደባቸውም ተዘግቧል።
ግጭቱ የተከሰተው ባለፈው በዓመት ጥር ወር ላይ ሲሆን የአንድ የአውሮፕላን ማረፊያ አጥር እየተገነባበት ወዳለው የዶንግ ታም መንደር ፖሊስ በገባበት ጊዜ ነበር።
የተቆጡ ግንባታውን የተቃወሙ የመንደሩ ነዋሪዎች ከፖሊሶች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተው በተከሰተ ግጭት ነው፤ ሦስት ፖሊሶችና በጡረታ ላይ የነበሩ የአካባቢው ባለስልጣን ህይወታቸው የጠፋው።
ቬትናም ውስጥ በመሬት ይዞታ ሳቢያ የሚከሰቱ አለመግባባቶች የተለመዱ ቢሆኑም ይህ ያህል የከፋ ጉዳት ግን እስከማስከተል አይደርሱም።
በአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በተያዘው በዚህ መሬት ላይ ቀደም ሲል የነበሩ ነዋሪዎች ተገቢውን ካሳ አላገኘንም በሚል ቅሬታ ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን፤ መንግሥት በመሬቱ ዙሪያ አጥር ሲያስገነባ ነበር ፖሊሶች ወደ አካባቢው ደኅንነት ለመጠበቅ የተሰማሩት።
ፖሊስ እንዳለው ነዋሪዎቹ የእጅ ቦምብ፣ ነዳጅ፣ ፌሮ ብረቶችና ሌሎች መሳሪያዎችን ተጠቅመው ነው ጥቃቱን የፈጸሙት። በፖሊሶቹ ላይ የተፈጸመው ግድያም ዘግናኝ እንደነበር ገልጿል።
ፖሊስ ያቀረበውን ክስ ነዋሪዎቹ የተቃወሙት ሲሆን ከነዋሪዎቹ ውስጥም ድብደባ ተፈጽሞባቸው ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉም ተናግረዋል።
በመሬት ይዞታው ሳቢያ ውዝግቡ የተጀመረው የቬትናም ጦር ሠራዊት በአካባቢው አየር ማረፊያ መገንባት ከጀመረበት ከሦስት ዓመት በፊት እንደሆነ ነው የተነገረው።
በዚህም ሳቢያ ነዋሪዎቹ 50 ሄክታር የሚደርስ ስፋት ያለው መሬት ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ከእነሱ ተውስዶ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ለሚተዳደረው ቬቴል ለተባለው የኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ በመሰጠቱ ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
የመንደሪቱ ነዋሪዎች ዜጎች ለተወሰደባቸው መሬት በተገቢው ሁኔታ ካሳ አልተሰጠንም በማለት በመቃወም፤ መሬታቸውን አሳልፈው ላለመስጠት ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።
የመጀመሪያው ውዝግብ የተከሰተው ከሦስት ዓመት በፊት አራት ሰዎች የመሬታቸውን መወሰድ በመቃወማቸው "የሕዝብን ሠላም በማናጋት" ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ሲሆን፤ ይህም ከፍተኛ ትኩረትንም አግኝቶ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በአጸፋው የመንደሩ ነዋሪዎች የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ 38 ባለስልጣናትን ለአንድ ሳምንት ይዘው አቆይተዋል። በኋላም በተደረገ ድርድር ለመለቀቅ በቅተዋል።
በኮሚዩኒስቷ ቬትናም ውስጥ ሁሉም መሬት የመንግሥት ሲሆን መንግሥት በፈለገ ጊዜ የትኛውንም መሬት ወስዶ ለሚፈልገው አገልግሎት ማዋል ይችላል።













