ሕንዳውያን ከልጅና የልጅ ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኑሮ ደረጃ መሻሻል፣ የከተሜነት መስፋፋት፣ ትምህርት እንዲሁም የባህል ለውጥ የሕንዳውያንን የቤተሰብ መዋቅር ይቀይረዋል ብለው የሚያምኑ አጥኚዎች ብዙ ናቸው።
እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። ሕንዳውያን ቤተሰቦች አሁንም ድረስ ተሰባስበው ነው የሚኖሩት።
ስለ ዘመናዊነት የሕንድ ቤተሰብ አወቃቀር ጥናት የሠሩት ዶ/ር ኤቲን ብሬቶን የሕዝብ ቁጥር ተመራማሪ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በአንድ ቤት የሚኖሩ ሕንዳውያን ቤተሰቦች ቁጥር ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ወዲህ አልቀነሰም።
ብዙ ጥንዶች አይፋቱም። ቤተሰብ የማይመሠርቱ ወጣቶች ጥቂት ናቸው። በጋራ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ቁጥርም አልቀነሰም።
ዶ/ር ኤቲን እንደሚሉት፤ ቤተሰቦች ወንድ ልጆቻቸውን ከዳሩ በኋላ አብረዋቸው ይኖራሉ።
ወንዶች አባቶቻቸው ከመሞታቸው በፊት ቤታቸውን ያሰናዳሉ። አባቶች ከሞቱ በኋላ እናትን የመንከባከብ ኃላፊነት የወንድ ልጆች ይሆናል።
ከሕንድ የተገኘ አሐዝ እንደሚያሳየው፤ ከ65 ዓመት በላይ ከሆኑ ሰዎች መካከል ከ50 በመቶ በላዩ ባለ ትዳር ናቸው። ወደ 45 በመቶው ሴቶች ደግሞ ባሎቻቸው ሞተዋል።
ወደ 80 በመቶ የሚጠጉ አረጋውያን ከልጆቻቸው ጋር ነው የሚኖሩት። ይህም በአንድ ቤት የሚኖሩ ቤተሰብ አባላት ቁጥር እየጨመረ መሆኑን እንደሚያሳይ ዶ/ር ኤቲን ያስረዳሉ።
ወጣቶች አሁንም ድረስ ከወላጆቻቸው ጋር ከሚኖሩበት ምክንያት አንዱ ሰዎች በሕይወት የሚኖሩበት እድሜ እየጨመረ መምጣቱ ነው።
በሕንድ በከተማ ቀመስ አካባቢዎች የሚኖሩት 35 በመቶው ዜጎች ብቻ ናቸው።
ማኅበራዊ ሳይንቲስቷ ዶ/ር አሊስ ኤቫንስ ስለ ጾታ እኩልነት ያጠናሉ። ሕንዳውያን በአንድ ላይ ተሰባስበው የሚኖሩት፤ አብሮነታቸው ከንግድ አንጻር አዋጭ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህም ሴቶች በሥራ እንዲሰማሩ እንደሚረዳ ያክላሉ።
በ1990ዎቹ አካባቢ የሕንድ ብቻ ሳይሆን የጃፓን፣ ኮርያ እና ታይዋን ቤተሰቦችም አብረው ይኖሩ ነበር።
“ምሥራቅ እስያውያን እንደ ሕንዳውያን ጥብቅ የቤተሰብ ትስስር ነበራቸው። ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ከቤተሰብ አባላት ውጪ ሥራ ሲቀጠር፣ ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ ሲፈልሱ እንዲሁም ሴቶች በተለያየ ዘርፍ ሲሰማሩ ትስስሩ ላልቷል” ይላሉ ዶ/ር አሊስ።
አሁን ላይ ልጆች ቤተሰቦቻቸውን የሚደግፉት አብረዋቸው እንዲኖሩ በመጋበዝ ሳይሆን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ነው።
በጃፓን፣ ኮርያ፣ ታይዋን እና ቻይና በርካታ ሴቶች በተለያየ የሙያ መስክ መሠማራተቸው ገቢያቸው እንዲጨምር አድርጓል።
ይህም በገንዘብ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉን የሚናገሩት ዶ/ር አሊስ፤ ሴቶች ትንሽ ልጅ ብቻ ስለሚወልዱ ሥራቸውን ማከናወን እንደሚቀጥሉም ያስረዳሉ።
የሕንድን የአገር ውስጥ ምርት ከግምት ብናስገባ ሌሎች መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮችም እንደ ሕንዳውያን ቤተሰቦች በጋራ እንደሚኖሩ መረዳት ይቻላል።
ስቲቨን ረግልስ እና ሚስቲ ሄገንስ የተባሉ አጥኚዎች በሰበሰቡት መረጃ መሠረት፤ በ15 ታዳጊ አገሮች ቤተሰቦች አብረው መኖራቸውን ቀጥለዋል።
ቲልሲ ፔታል የተባሉት የማኅበረሰብ አጥኚ ሕንድ ውስጥ የቤተሰብ መዋቅርን ይህ ነው ብሎ መተርጎም አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜም አለ ይላሉ።
“ቤተሰቦች ከአንድ ልጃቸው ቤት ወደ ሌላው ይዘዋወራሉ። ከልጅ ልጆቻቸው ጋርም ጊዜ ያሳልፋሉ። ልጆቻቸው ወደ ሌላ አገር ቢሄዱም ተከትለዋቸው ይሄዱና የልጅ ልጆቻቸውን ይንከባከባሉ” ይላሉ።
በብዛት ከልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት አቅመ ደካማ ቤተሰቦች እንደሆኑ አጥኚው ይናገራሉ።
ከጎርጎሮሳውያኑ 2000 ወዲህ አርሶ አደር ቤተሰቦች ከዩኒቨርስቲ ምሩቃን በበለጠ ከልጆቻቸው ጋር እየኖሩ ነው። ይህም ጉዳዩ ከምጣኔ ሀብት ጋር ተያያዥነት እንዳለውም ይጠቁማል።
በሌላ በኩል ሕንድ ውስጥ ልጆች የሚዳሩት በወላጆቻቸው ስምነነት እንጂ በጥንዶቹ ፍቃድ አይደለም። ይህ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ ነው።
ሴቶች የትዳር አጋራቸውን መምረጥም እየጀመሩ መጥተዋል። በተያያዥ አንዳንድ እድሜያቸው የገፋ ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር ሳይሆን ብቻቸውን መኖር ምርጫቸው ነው።
አጥኚው እንደሚሉት፤ የልጆች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ አንድ ቤተሰብ ከሌላው የቤተሰብ አባላት ጋር በትስስር የሚኖርበት ባህልም እየሳሳ ሊሄድ ይችላል።
ቤተሰቦች ወንድ ልጆቻቸው ትዳር ሲመሰርቱ አብረዋቸው የመኖር ልማድ አላቸው። ወንድ ልጅ የሌላቸው ቤተሰቦች ሴት ልጆቻቸው ቤት ይኖራሉ? የሚለው ሌላው የአጥኚው ጥያቄ ነው።
ምናልባትም በሕንድ ቤተሰቦች መዋቅር ላይ ለውጥ የሚያመጡት የተማሩት የማኅበረሰቡ ክፍሎች ሳይሆን አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም አጥኚው ያምናሉ።












