ኢራን፤ በኢራቅ የሚገኝ የአሜሪካ ወታደሮች መኖሪያን መደብደቧ ተሰማ
በኢራቅ የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ጦር መኖሪያዎች ከኢራን በተወነጨፉ የባሌስቲክ ሚሳኤሎች መደብደባቸው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ገለፀ።
የኢራን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ጥቃቱ የተፈፀመው ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የኢራንን ከፍተኛ የጦር አበጋዝ ከገደለች በኋላ ለእርሱ ምላሽ ነው ብሏል።
ፔንታገን በኢራቅ የሚገኙ ሁለት የጦር ሰፈሮች መደብደባቸውን አስታውቋል።
የጦር ሰፈሮቹ የሚገኙት በኢብሪልና አል አሳድ መሆኑም ታውቋል። እስካሁን ግን የተጎዱ ወይንም የሞቱ ስለመኖራቸው የታወቀ ነገር የለም።
"በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ንብረቶች ላይ ጥቃት መድረሱን አረጋግጠናል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ መረጃው እንዲደርሳቸው ተደርጓል። ጉዳዩን ከብሔራዊ ደህንነት ቡድን ጋር በመሆን በቅርበት እየተከታተልነው እንገኛለን" ያሉት የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ስቴፈኒ ግሪሻም ናቸው።
የኢራን ሪቮሊውሺነሪ ጋርድ ጥቃቱ የተፈፀመው ለጄነራል ሶሌይማኒ ግድያ ምላሽ መሆኑን አስታውቋል።
በኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የተነበበው መግለጫ " የአሜሪካ አጋሮችን በአጠቃላይ፣ የጦር መንደራቸውን ለአሸባሪ ጦር ሰፈርነት የፈቀዱትን፣ ከኢራን በተቃራኒ ለሆነ ተግባር ግዛታቸውን መነሻ የሆነን በሙሉ አስጠንቀቅነል" የሚል ዐረፍተ ነገር ይዟል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ በኋላ ላይ በትዊተር ገጻቸው ላይ በጻፉት መልዕክት ጥቃቱን የፈፀሙት ራስን ለመከላከል መሆኑን ገልፀው ግጭቱ ወደ ጦርነት እንዲያመራ ኢራን ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 1
ከዚያ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትዊተራቸው ላይ "ሁሉም ነገር መልካም ነው" በማለት በርግጥ እስካሁን ድረስ የደረሰውን ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ እንዳላጣሩ ተናግረዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ, 2
ጥቃቱ የተፈፀመው የሶሌይማኒ ቀብር ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላ መሆኑን የገለፀው አል ማይዲን የተሰነው ቴሌቪዥን ጣቢያ ሁለተኛው ጥቃት ኢርቢል ላይ የደረሰው የመጀመሪያው አል አሳድን ከመታ ከአጭር ሰዓት በኋላ ነው ሲል ገልጿል።
ቃሲም ሶሌይማኒ ማን ነበሩ?
ከእ.አ.አ. 1998 ጀምሮ ሜጀር ጀነራል ሶሌይማኒ የኢራን ኩድስ ኃይልን ሲመሩ ቆይተዋል። ይህ ኃይል ከሃገር ውጪ የሚፈጸሙ ሚስጥራዊ ኦፕሬሽኖችን የሚያከናውን ነው።
ጀነራሉ በኢራቅ ውስጥ አይኤስ እና አል-ቃይዳን በመዋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪም፤ እኚህ የሽብር ቡድኖች እግራቸውን በኢራን እንዳይተክሉ ተከታትለው ድባቅ የመቷቸው ጀነራል ሶሌይማኒ ነበሩ ተብሏል።
ጀነራሉ የሚመሩት ኃይል በሶሪያ ግጭት ውስጥ ተሳትፎ እንዳለው አምኗል። ለፕሬዝደንት በሽር አል-አሳድ ታማኝ ለሆኑ ወታደሮች የጦር ምክር ይሰጣል። እንዲሁም ለባሽር አል-አሳድ ታማኝ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሺያ ሙስሊሞችን አስታጥቋል። በኢራቅ ደግሞ አይኤስን እየታገሉ ለሚገኙ ለሺያ ሙስሊም ሚሊሻዎች ድጋፍ ያደርጋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የተከሰቱት ግጭቶች ጀነራሉ ኢራን ውስጥ እጅግ ዝነኛ ሰው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ጀነራል ሶሌይማኒ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የኢራን ከፍተኛ የጦር ሽልማት ተቀብለዋል።
አሜሪካ በበኩሏ ጀነራሉ የሚመሩት የኩድስ ኃይል በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አሜሪካን በጠላትነት በመፈረጅ በሽብር መናጥ ለሚፈልጉ ኃይሎች ፈንድ፣ ሥልጠና እና የጦር መሳሪያን ጨምሮ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ስትል ትወነጅላለች።
አሜሪካ እንደምትለው ከሆነ ይህ የኩድስ ኃይል ድጋፍ ከሚያደርግላቸው ኃይሎች መካከል፤ የሌባኖሱ ሄዝቦላ እንዲሁም የፍልስጤሙ እስላማዊ ጅሃድ ተጠቃሽ ናቸው።
የቀድሞ የሲአይኤ አለቃ የአሁኑ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ የኢራንን አብዮታዊ ጥበቃ እና ኩድስ ኃይሉን "የሽብር ቡድን" ሲሉ ከወራት በፊት ፈርጀውት ነበር።
















