ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክ፡ ትልቁ ማሕበራዊ ሚድያ ከአሜሪካ ምርጫ በፊት ፖለቲካዊ ማስታወቂያዎችን ሊያግድ ነው
ፌስቡክ በጎርጎሮሳውያኑ ሕዳር 3 ከሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ በፊት ባሉት ሰባት የመጨረሻ ቀናት ውስት ምንም አይነት ፖለቲካዊ ማስታወቂያዎችን እንደማያስተናግድ አስታውቋል።
ነገር ግን ድርጅቱ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ኢላማ ያደረጉና አሁን ያሉ ማስታወቂያዎች እንዲሄዱ የሚፈቅድ ይሆናል።
የፌስቡክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ውሳኔውን ያሳወቀው በፌስቡክ ላይ ነው።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በመልእክቱ ''ከምርጫው ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ክፍፍሎች ምከንያት አለመረጋጋት እንዳይፈጠር ስጋት አለኝ'' ብለዋል።
አክሎም የምርጫው ውጤት ይፋዊ በሆነ መንገድ ከመገለጹ በፊት ማሸነፋቸውን በፌስቡክ የሚገልጹ እጩዎችንም ቢሆን በቅርበት እንደሚከታተሉና እንደሚቆጣጠሩ ገልጿል።
የማህበራዊ ሚዲያው ፌስቡክ በቅርብ ዓመታት አነስተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ስለሚመለከቷቸው በማለት ፖለቲካዊ ማስታወቂያዎችን ዝም ብሎ ለቋል የሚል ክስ ሲቀርብበት ነበር።
የሞዚላ ፋውንዴሽን እንዳስታወቀው እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው ሐሰተኛ መረጃዎችን ያለምንም ጠያቂ እንዲያሰራጩ እድል ይፈጥራል።
ፌስቡክ ፖለቲከኞች በማስታወቂያቸው ውስጥ የሚናገሩት ነገር እውነት ይሁን ውሸት አይጣራም ነበር ማለቱ ነገሮችን አወዛጋቢ አድርጎ ነበር።
ይህ አዲሱ የፌስቡክ እርምጃ ምናልባትም ወደፊት ከምርጫ ጋር የተገናኙ ነገሮችን እንዴት እንደሚያስተናግድ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል።
ፌስቡክ ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ካሮሊና መራጮች ሁለት ጊዜ እንዲመርጡ መልዕክታቸውን ያስተላለፉበት ተንቀሳቃሽ ምስል ሕገወጥ በመሆኑ አጠፋዋለሁ ብሏል።
በተጨማሪም ግራ መጋባትን ሊፈጥሩ የሚችሉና ማረጋገጫ የሌላቸው መልዕክቶች የተላለፉባቸው የፕሬዝዳንቱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዲጠፉ ይደረጋሉ ያለ ሲሆን ፌስቡክ ምስሎቹ የድርጅቱን ፖሊሲዎች የሚጣረሱ ናቸው ብሏለቸዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ምርጫው ሊጭበረበር እንደሚችል ሲገልፁ ነበር።
ነገር ግን ምንም አይነት ማጭበርበር ሊኖር ስለመቻሉ ተቀባይነት ያለው ማስረጃ እስካሁን አልተገኘም።
''ምርጫው ከዚህ በፊት እንደተለመደው የምናስተናግደው ነገር አይደለም'' ብሏል ማርክ ዙከርበርግ።
'' አገራችን እንዲህ በተከፋፈለችበት በዚህ ወቅት የምርጫ ውጤቱ እስከሚታወቅ ድረስ ቀናት አልያም ምናልባት ሳምንታት ሊፈጅ ይችላል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ የሲቪል አለመረጋጋትን ሊያስከትል ይችላል''
በፌስቡክ የሚለቀቁ ተባራሪ ወሬዎችንና ሆነ ተብለው የሚለቀቁ አሳሳች መልዕክቶችን ለመቆጣጠር ደግሞ ድርጅቶ ተከታታተይ የሆኑ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል።
• ከምርጫው በፊት ባሉት ሰባት የመጨረሻ ቀናት ምንም አይነት ፖለቲካዊ ማስታወቂያዎችን ድርጅቱ አይቀበልም
• ሰዎች በምርጫው የሚሳተፉ ከሆነ በኮቪድ-19 እንደሚያዙ የሚገልጹ መልዕክቶች ይሰረዛሉ
• የምርጫውን ውጤት ሕጋዊ መሰረት ሊያሳጡ የሚችሉ መልዕክቶችም ገደብ ይበጅላቸዋል
• እንዲሁም የመጨረሻ የምርጫው ውጤት ሳይገለጽ እንዳሸነፉ የሚገልጹ እጩዎችን መልዕክትም ይቆጣጠራል
'ሚዲያ ማተርስ ፎር አሜሪካ' የተባለው ድርጅት ግን የፌስቡክን ውሳኔ ተራ እውቅናን ለማግኘትየተደረገ ነው ነው ብሎታል።
በሰሜን ካሮላይና ቻፔል ሂል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳንኤል ክሬስ በበኩላቸው ከምርጫው በፊት ካሉት የመጨረሻ ሰባት ቀናት በፊት ፖለቲካዊ ማስታወቂያቸውን የሚያስነግሩ ሰዎች ደግመው በምርጫው ሳምንትም ተመሳሳይ መልዕክት እንዲለቁ የሚፈቀድላቸው ከሆነ ትርጉም የለውም ብለዋል።