በኡበር መሳፈር ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ ጭምብል ያጠለቁበትን ፎቶ ይላኩ

ታትሟል

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የህዝብ ትራንስፖርት መሳፈር ስጋት በሆነበት ወቅት ኡበር በመኪኖቹ ውስጥ የሰልፊ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) እንዲገጠም ውሳኔ ላይ ደርሷል።

ይህም መተግበሪያ ደንበኞች በመኪኖቹ ውስጥ ከመሳፈራቸው በፊት ጭምብል ማጥለቅ አለማጥለቃቸውን አሽከርካሪዎቹ እንዲያውቁ ለማድረግ ነው።

በተለይም ከዚህ ቀደም ጭምብል ሳያደርጉ ለመሳፈር የሞከሩ ደንበኞችን ዝርዝር የወጣ ሲሆን እነዚህ ግለሰቦች ጭምብል አጥልቀው ፎቶ ካልላኩ መሳፈር አይችሉም።

ተሳፋሪዎች ጭምብል ማጥለቅ አለማጥለቃቸውን የሚለየው መተግበሪያ በአሜሪካና ካናዳ መጀመሪያ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ከመስከረም መጨረሻ በኋላ ግን በተለያዩ የአለም ክፍሎችም ተፈፃሚ ይሆናል።

ይህም መተግበሪያ አሽከርካሪዎችንም ሆነ ተሳፋሪዎችን ከኮሮናቫይረስ መጠበቅ እንደሚያስችልም የኡበር ኃላፊ ዳራ ኮስሮውሻሂ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል

ይህ መተግበሪያ የፊት ገፅታን ለማወቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንደማይጠቀም የተገለፀ ሲሆን ፊት ላይ ያለውን ሌላ ቁስ (በዚህ ሁኔታ ጭምብልን) መለየት የሚያስችልም ነው ተብሏል።

መተግበሪያ ፎቶዎቹን ለ96 ሰዓታት ያህል ቢያስቀምጥም ከዚያ በኋላ ግን በቋሚነት ያጠፋቸዋል።

በአሁኑ ወቅት አሽከርካሪዎች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ጭምብል አጥልቀው 'ሰልፊ' መነሳት ይጠበቅባቸዋል።

በመኪናው ውስጥ ያለው መለያ አሽከርካሪዎቹ ጭምብል ማጥለቃቸውን መለየት ካልቻለ ደንበኞችን ማሳፈር እንዳይችሉ ያግዳቸዋል።

ኡበር "ጭምብል ከሌለ መሳፈር የለም" የሚለውን ዘመቻውን በግንቦት አጋማሽ ካስተዋወቀ በኋላ አሽከርካሪዎችም ሆነ ተሳፋሪዎች ጭምብል እንዲያጠልቁ አስገዳጅ አድርጎታል።

ድንገት አሽከርካሪዎችም ሆነ ተሳፋሪዎች ጭምብል ካላጠለቁ ያለምንም ክፍያ ወዲያውኑ ጉዞውን መሰረዝም ይቻላል። የኩባንያውን ትዕዛዝ ሳያከብሩ የቀሩትም አካውንታቸው ይታገዳል።

ወረርሽኙን ተከትሎ የኡበር አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቆለ ሲሆን በተለይም በአሜሪካ አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥ መመሪያ ከፍተኛ ጫናን አሳርፏል ተብሏል።

ኡበር ለአሽከርካሪዎቹ ጭምብል፣ የእጅ ጓንት፣ የፀረ-ተህዋሲያንን ግዥ 50 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቱን ያሳወቀ ሲሆን፤ በአለም ላይ ላሉት 1.4 ሚሊዮን አሽከርካሪዎቹም ጭምብል አከፋፍያለሁ ብሏል።