በመጪው ጥቅምት ስታዲየሞች ለተመልካቾች ክፍት ሊደረጉ ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታዎችንና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮችን ለመመልከት ከመጪው ጥቅምት ጀምሮ ወደ ስታዲየም መግባት ሊፈቀድላቸው እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ተናገሩ።
ከሦስት ወር በኋላ ስታዲየሞችን ለተመልካች ክፍት ለማድረግ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ሙከራዎች ማድረግ የሚጀመር ሲሆን ነገር ግን የትኛውም ስታዲየም የሚከፈተው የኮሮናቫይረስ መከላከያ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ ብቻ ነው።
እግር ኳስን ጨምሮ አንዳንድ የስፖርት ውድድሮች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ለወራት ከተቋረጡ በኋላ በዝግ ስታዲየሞች መካሄድ ጀምረዋል።
"የስፖርት ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ስታዲየሞችን በመሰሳሉ በርካታ ሕዝብ የሚታደምባቸው ስፍራዎችን ለመክፈት የሚያስችል ሙከራዎችን እናደርጋለን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ዛሬ ተናግረዋል።
ከጥቅምት ወር ጀምሮም ስታዲየሞች ውስጥ ተመልካቾች እንዲገቡ ለማድረግ ወረርሽኙ የማይተላለፍባቸው ሁኔታዎችን ለማረጋገጥ አሁን የሚደረገው ፍተሻ የተሳካ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ይህ ለውጥ ሲደረግ ከኮሮናቫይረስ ነጻ በሆነና በአስተማማኝ ሁኔታ መሆን ያለበት ሲሆን ለዚህም ነሐሴ ላይ የሚደረገው ሙከራ ውጤታማ መሆን ይኖርበታል" ብለዋል።
ከመጋቢት በኋላ ተቋርጠው የነበሩት የአገር ውስጥ የውድድር ስፖርቶች በሰኔ ወር የተጀመሩ ሲሆን፤ የፕሪሚየር ሊግና የእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ ጨዋታዎች በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በተከታታይ ተጀምረዋል።
ዓለም አቀፍ የክሪኬት፣ የጎልፍ፣ የፈረስ ግልቢያ ውድድሮችና ሌሎችም በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መካሄድ ጀምረዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአምስት ወራት ውስጥ 45 ሺህ ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ292 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል።














