የቀድሞው የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ አዛዥ የአማራ ክልል ፖሊስን እንዲመሩ ተሾሙ

ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ ይልማ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞው የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም) አዛዥ ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ ይልማ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ።

ላለፈው አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ገደማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሆነው የሰሩት ዶ/ር ዘላለም መንግሥቴ ወደ ቀድሞ ኃላፊነታቸው እንደተመለሱ ተገልጿል።

አዲሱን አዛዥ ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ የሾሙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ መሆናቸውን የክልሉ ፖሊስ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

ላለፉት ሦስት ዓመታት ግጭት ውስጥ ያለውን የአማራ ክልል የፖሊስ ኃይል የመምራት ኃላፊነትን የተረከቡት ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ወታደራዊ መኮንን ናቸው።

ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ ይህንን ኃላፊነት የተረከቡት፣ መንግሥት በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ኃይሎች "ጽምዶ" በሚል በሚጠራው ጥምረት አማካኝነት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ትብብር መፍጠራቸውን እየገለጸ ባለበት ወቅት ነው።

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የተባለውን ታጣቂ ቡድን የሚመሩት ዘመነ ካሴ 'ሌ ቴምፕስ' ለተባለው የሲውዘርላንድ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ የትግራይ ኃይሎችን ጨምሮ ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር ለመተባባር "ለስምት ወራት ገደማ" ውይይት መደረጉን ተናግረዋል። የትብብሩ አካል ተብለው ከተጠቀሱት መካከል "የጉሙዝ፣ በርታ፣ ሶማሊ እና ኦሮሞ ኃይሎች" ይገኙበታል።

በክልሉ የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚደረገው ጥረት በዋነኛነት በመከላከያ ሠራዊት የሚመራ ሲሆን፣ በክልሉ ፖሊስ ሥር የሚገኙት የአድማ ብተና ኃይሎችም ተሳትፎ ያደርጋሉ።

አዲሱ የክልሉ ፖሊስ አዛዥ ወደዚህ ኃላፊነት ከምጣታቸው አስቀድሞ የመከላከያ ሠራዊቱ ጤና ዋና መምሪያን በኃላፊነት እየመሩ ነበር። የመከላከያ የሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ እና የመከላከያ ካውንስል አባል በመሆንም አገልግለዋል።

ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በቀጣናዊ የመከላከያ ሠራዊት ስምሪት ላይ በአመራርነት ሰርተዋል።

ከየካቲት 2011 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 2012 ድረስ አልሸባብ ሶማሊያ ላይ የደቀነውን ስጋት ለመቀነስ በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ የተቋቋመውን የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) በአዛዥነት መርተዋል።

ከመጋቢት 1999 ዓ.ም አንስቶ ለአስራ አምስት ዓመታት የቆየው ይህ ተልዕኮ፣ መጋቢት 2014 ዓ.ም የቆይታ ጊዜውን አጠናቅቆ፣ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) መተካቱ ይታወሳል።

ይህ የሽግግር ተልዕኮም ከ2017 ጥር ጀምሮ 'አውሶም' በተባለው የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ መተካቱ ይታወሳል። አውሶም በመጪው ታኅሳስ ወር የቆይታ ጊዜው ያበቃል።

ለዚህ ተልዕኮ ወታደር የሚያዋጡ አገራት ባለፈው ሐምሌ ላም በዩጋንዳ ካምፓላ ውስጥ ባካሄዱት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙት አዛዥ ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ ነበሩ።

ሌተናንት ጄነራል ጥጋቡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በፖሊስ አዛዥነት የተሾሙ ሁለተኛው ወታደራዊ መኮንን ናቸው።

ባለፈው መጋቢት የመከላከያ የምድር ኃይል ዋና አዛዥ እንዲሁም የሠራዊቱ መረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ሌተናንት ጄነራል አስራት ደኔሮ የአዲስ አበባ ፖሊስን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሾማቸው ይታወሳል።

ከመጋቢት 2017 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሆነው የቆዩት ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግሥቴ፣ ከዚህ ቀደም ወደ ነበሩበት የፌደራል ፖሊስ ምክትል ዋና ኮሚሽነርነት ኃላፊነት መመለሳቸውን የክልሉ ፖሊስ መረጃ ያሳያል።