ሪያል ማድሪድ ለ34ኛ ጊዜ ላ ሊጋውን ማሸነፉን አረጋገጠ

Real Madrid celebrate

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሪያል ማድሪድ ለ34ኛ ጊዜ ላ ሊጋውን ማሸነፉን አረጋገጠ
ታትሟል

ሪያል ማድሪድ ትናንት ምሽት ቪላሪያልን ማሸነፉን ተከትሎ የላ ሊጋውን ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል።

የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ከሶስት ዓመት በኋላ ላ ሊጋውን ማሸነፉ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ከማንሳት በላይ ደስታ እንደፈጠረለት ተናግሯል።

ማድሪድ የላ ሊጋውን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋገጠው ካሪም ቤንዜማ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ቪላሪያልን ማሸነፉን ተከትሎ ነው።

በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የስፔን ሊግ ከተመለሰ በኋላ ማድሪዶች ያደረጓቸውን 10 ጨዋታዎች በሙሉ ማሸነፍ ችለዋል። በዚህም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ባርሴሎና በ7 ነጥቦች እርቀው ነው ዋንጫ ማንሳታቸውን ያረጋገጡት።

"ዛሬ ለእኔ ልዩ ቀን ነው። ብዙ ነገር ካሳለፍን በኋላ፣ ለሦስት ወራት ሊጉ ተቋርጦ ቆይቶ ተመልሰን ያሳካነው ነገር ድንቅ ነው" ብሏል ዚዳን።

ሳንቲያጎ በርናቦ ስታዲየም በእድሳት ላይ ስለሚገኝ ማድሪዶች ያለፉትን ጥቂት ጨዋታዎች ሲያካሂዱ የነበረው በሁለተኛው ስታዲየማቸው ነው። በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት እንደተለመደው ተጫዋቾች ከድል በኋላ በክፍት አውቶብስ ላይ ሆነው በማድሪድ ከተማ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተሰባሰበው ድላቸውን ማጣጣም እንደማይችሉ ከአሁኑ ግልጽ ተደርጓል።

"ለሁላችንም ያልተለመደ ነገር ነው" ያለው ዚዳን "ከደጋፊዎቻችን ጋር በአንድ ላይ ሆነን ደስታችንን ብንገልጽ ደስ ይለኝ ነበር። ይሁን እንጂ እርግጠኛ ነኝ ሁሉም ደጋፊ በየቤቱ ደስተኛ ነው" ሲል ተናግሯል።