የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አብን በምክክሩ ሂደት ላይ የደረሰበትን ድምዳሜ እንደማይቀበለው ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian National Dialogue Commission
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ በምክክሩ ሂደት ላይ "ከተራ የአሠራር ግድፈት" የዘለሉ "ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል" ሲል ያቀረበውን ክስ ውድቅ አደረገ።
አብን ቅዳሜ ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በሀገራዊ ምክክሩ "ገዢው አካል መዋቅራዊ ጥሰቶችን" እንደፈጸመ በመጥቀስ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ "የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅ እና ፍላጎት በአግባቡ ሳይወከል" ታልፏል ብሎ ነበር።
ፓርቲው በዚሁ መግለጫው ላይ ሂደቱ ውስጥ ታይተዋል ያላቸውን "አግላይ እና አፋኝ አካሄዶች" በተመለከተ ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በደብዳቤ አቤቱታ ማቅረቡን ገልጿል።
ይህንን የአብን መግለጫ በሚመለከት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሰኞ ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ የምክክር ሂደቱ "አካታች እና አሳታፊ አይደለም የሚለውን የአብን አቋም ኮሚሽኑ ተገቢውን ምርመራ እና ማጣራት" ማድረጉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ አክሎም ባደረገው ምርመራ እና ማጣራት የፖለቲካ ፓርቲውን ድምዳሜ "የማይጋራው" መሆኑንም አስታውቋል።
አብን ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ በምክክር በሂደቱ ውስጥ የታየው ሁኔታ ከተራ የአሠራር ግድፈት ወይም ከመደበኛ የፓለቲካ ልዩነት የዘለለ ሆኖ እንዳገኘው ጠቅሶ ነበር።
በምክክር ሂደቱ ላይ ተፈጽመዋል ያላቸውን "ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች" የሀገራዊ ምክክሩን "ተዓማኒነት፣ አካታችነት፣ ገለልተኝነት እና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚስገቡ" እንደሆኑም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ኮሚሽኑ ዛሬ ለአብን ቅሬታ በሰጠው ምላሽ ደግሞ ባለው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ሂደቱን "በነፃነት፣ በገለልተኝነት፣ በአካታችነት እና በአሳታፊነት ለማስኬድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ" እንደሚገኝ አስታውቋል።
አብን በምክክሩ ሂደት ላይ ለታዩት "መዋቅራዊ ጥሰቶች፣ ጫናዎች እና ወገንተኛ አካሄዶች" ተጠያቂ ያደረገው አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘውን ገዢውን ፓርቲ ነው።
አብን ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ "መንግሥታዊ መዋቅሮችን የአንድን ቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የማዋል ጥረት እንደሚደረግ በስፋት አስተውለናል" ብሏል።
"በገዢው አካል" ተፈጽመዋል የተባሉት እነዚህ ድርጊቶች "ሂደቱ የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት" መደቀናቸውንም አስረድቷል።
ኮሚሽኑ በበኩሉ "የምክክሩ ሂደት የማንኛውም ፓርቲ፣ የመንግሥት አካል ወይም የተለየ ቡድን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚውል መድረክ አይደለም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችም እንደነበሩ ያስታወሰው የኮሚሽኑ መግለጫ፣ በየመካከሉ በኮሚሽኑም ይሁን በተመካካሪዎች በኩል የተስተዋሉ ጉድለቶች እና የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በአግባቡ ለመፍታት እንዲሁም ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን አብራርቷል።
አብን በምክክሩ ሂደት ከሌሎች ተወካዮች ጋር በመሆን "ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው" ያለው ኮሚሽኑ በቀሪው የምክክር ሂደትም በንቃት መሳተፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ የማንኛውንም ተመካካሪ አቤቱታ እና ቅሬታ በቀላሉ የሚያልፈው ጉዳይ አለመሆኑን ገልጾ፣ "አብንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ መሠረት ምላሽ እየሰጠ ይገኛል" ብሏል።
ኮሚሽኑም የሁሉንም ዜጎችና ተመካካሪዎች ድምፅ በእኩልነት ለማዳመጥ እና ሂደቱን በነፃነት እና በገለልተኝነት ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ከመላው አገሪቱ እንዲሁም በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተወከሉ ተመካካሪዎች የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ ከቀረቡ እና ተሳታፊዎችን ካላግባቡ የውይይት አጀንዳዎች መካከል የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ ነው።
አብን በአገራዊ ምክክሩ አዲስ አበባን በተመለከተ የከተማዋ ሕዝብ እንደ ዋና ባለቤት ሳይቆጠር መታለፉ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሷል።
አብን በመግለጫው ላይ "የአዲስ አበባ ከተማን መሬት እና አስተዳደር በተናጠል የመቆጣጠር ፍላጎት ታይቷል" ያለው አብን፣ የከተማዋን "ገጽታ ወደ አግላይ ዘውጌያዊነት መለወጥ" የለበትም የሚል አቋም እንዳለው አስታውቋል።
ፓርቲው እስካሁን ድረስ እነዚህን መሠረታዊ ግድፈቶች ለማረም የተወሰደ አዎንታዊ እርምጃ አለመኖሩን ጠቅሶ፣ ወደፊትም "ገዢው አካል የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርገው ስልታዊ ተፅዕኖ እና ጣልቃ ገብነት እየጨመረ እንደሚሄድ አሁናዊ ሁኔታዎች ያመላክታሉ" ሲል ስጋቱን ገልጿል።
አብን "አንድ ወገን ብቻውን የሚወስንበት፣ አግላይ እና አምባገነናዊ ሥርዓትን የመጫን እንቅስቃሴ የማይቆም ከሆነ" ለሂደቱ "ዕውቅና የማይሰጥ እና የማይተባበር መሆኑን" በመግለጫው አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ለአብን ቅሬታዎች ምላሽ በሰጠበት መግለጫ ላይ ሀገራዊ ምክክሩ "የአንድ ወገን ድል ወይም የሌላ ወገን ሽንፈት አይደለም" በማለት "ኢትዮጵያ የምትሻገርባቸውን የጋራ መፍትሔዎች ለማፈላለግ የሚያግዝ፤ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት ነው" ብሏል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የለያቸውን በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች የተከፋፈሉት ስምንት ቡድኖች፣ እያንዳንዳቸው በተለያዩ ደረጃዎች ሲያደርጉ የነበሩትን ውይይት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ቡድኖቹ "ያዘጋጇቸው እና የተስማሙባቸው ምክረሃሳቦች" አራት ሺህ አባላት ላሉት ጠቅላላው ጉባኤ ከመቅረቡ በፊት፣ የተናበበ፣ የተጣጣመ እና የተደራጀ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።















