አብን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁለት ኮሚሽነሮች በጉባዔው አጀንዳዎች ላይ እጃቸውን ለማስገባት ሞክረዋል ሲል ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of innovation and Technology
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁለት ኮሚሽነሮች በምክክር ጉባዔው አጀንዳዎች ላይ በቀጥታ እጃቸውን በማስገባት ተጽዕኖ ለማድረግ ሞክረዋል ሲል ከሰሰ።
ፓርቲው ይህንን ያለው ነሐሴ 11፣ 2018 ዓ.ም. ኮሚሽኑ አብን አቅርቧቸው ለነበሩ ቅሬታዎች የሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ነው።
አብን በመግለጫው ሁለት ኮሚሽነሮች በቀጥታ በምክክሩ ሂደት ውስጥ "በተለይም በከተሞች አጀንዳ ውስጥ" እጃቸውን ማስገባታቸውን ጠቅሶ፣ "የተሳታፊዎችን ፍላጎት ለማስቀየር እና ተጽዕኖ ለማሳደር" ሙከራ ማድረጋቸውን በተደጋጋሚ መታዘቡን አመልክቷል።
አብን ሰኞ ምሽት ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ ያቀረባቸውን አቤቱታዎች ተከትሎ ኮሚሽኑ ጥሰት ፈጸሙ የተባሉ የተወሰኑ አካላትን ለይቶ ከኃላፊነት ማንሳቱን ጠቅሷል።
ይህ እርምጃ የተሟላ አይደለም ያለው ፓርቲው "በተለይም የሁለቱ ኮሚሽነሮችና የጥቂት አስተባባሪዎች አሉታዊ ጣልቃ ገብነት" መቀጠሉን አስታውሷል።
ፓርቲው አክሎም "የመንግሥት አካላት አሠራር ሙሉ በሙሉ አለመታረሙ" ቅሬታ ፈጥሮብናል ሲል በመግለጫው ላይ ዳግም አቅርቧል።
አብን ቅዳሜ ዕለት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ከተራ የአሠራር ግድፈት የዘለሉ ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል ሲል ቅሬታውን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቆ ነበር።
አክሎም ገዢው አካል መዋቅራዊ ጥሰቶችን ፈጽሟል ሲል የከሰሰው አብን፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ "የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅ እና ፍላጎት በአግባቡ ሳይወከል" ታልፏል ብሏል።
ኮሚሽኑ ለዚህ የአብን ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት ሰኞ ነሐሴ 11፣ 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የቀረበለትን አቤቱታ መመርመሩን እና ማጣራቱን ገልጾ፣ በፓርቲው ድምዳሜ እንደማይስማማ አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎ አብን ባወጣው ሌላ መግለጫ ላይ ኮሚሽኑ መሠረታዊ ሥጋቶቹንና ቅሬታዎቹን "አቅጣጫ የሚያስቱ" እና "ተጨባጭ" እና "ተደጋጋሚ" አቤቱታዎቹን ከግንዛቤ ያላስገባ ምላሽ ሰጥቷል ሲል ወቅሷል።
ኮሚሽኑ ያቀረብነውን ቅሬታ "አጠቃላይ የሂደት ክፍተት" አስመስሎ ለማቅረብ ሞክሯል ያለው ፓርቲው፣ የምክክር ኮሚሽኑ የመደባቸው አንዳንድ ባለሙያዎች "አድሏዊ" እና "ተገቢ ያልሆኑ" ሀሳቦችን ሲያራምዱ ነበር ሲል ከስሷል።
አብን፣ የተወሰኑ አስተባባሪዎች ደግሞ የፓርቲው ተወካዮችና ሌሎች ተሳታፊዎች መሠረታዊ አቋሞቻቸውንና ሀሳቦቻቸው እንዳያቀርቡ "በስልታዊ" መንገድ አፈና ሲፈጽሙ ነበር ሲል ወንጅሏቸዋል።
ሆኖም የኮሚሽን አባላትም ሆነ ኮሚሽኑን እንደ ተቋም "በጅምላ ጥፋተኛ ናቸው" ወይም "ገለልተኛ አይደሉም" የሚል ቅሬታ ወይም ድምዳሜ አለማቅረቡን አብን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
የፓርቲው መሠረታዊ ቅሬታ የቀረበው በገዥው ፓርቲ እንዲሁም በአንዳንድ ደጋፊዎቹ በኩል በተፈጸሙ "ያልተጠበቁና ያልተለመዱ የአሠራር ጥሰቶች" ላይ መሆኑን አስታውሷል።
"አንዳንድ የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የምክክሩን ሂደት በማዛባት፣ አጀንዳዎችን በበላይነት ለመጫን እና በተሳታፊዎች ላይ ያልተገባ ተጽዕኖ ለመፍጠር" ጣልቃ በመግባት ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ተግባራት መፈጸማቸውን በመግለጫው ላይ አስፍሮ ይህንንም ለኮሚሽኑ ማስታወቁን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ፓርቲው ያቀረበውን ቅሬታ "አጠቃላይ የሂደት ክፍተት" አስመስሎ ለማቅረብ ተሞክሯል ካለ በኋላ "ተለይተው የታወቁ ሁለት ኮሚሽነሮች" በቀጥታ በምክክሩ ሂደት ውስጥ እጃቸውን ለማስገባት እና የተሳታፊዎችን ሃሳብ ለማስቀየር መሞከራቸውን ጠቅሷል።
አብን የኮሚሽነሮቹን ስም በመግለጫው ላይ አልጠቀሰም።
ኮሚሽኑ ሲቋቋም ተመርጠው የነበሩት 11 ኮሚሽነሮች ቢሆኑም ሁለቱ በፈቀዳቸው በመልቀቃቸውን እና አንዱ በሞት በመለየታቸው የተነሳ ስምንት ኮሚሽነሮች የምክክር ሂደቱን በመምራት እያገለገሉ ይገኛሉ።
አብን በመግለጫው ኮሚሽነሮቹ በተደጋጋሚ ተጽዕኖ አሳድረዋል ሲል ውንጀላውን ያቀረበው "በተለይም በከተሞች አጀንዳ" ውስጥ ነው።
በተጨማሪም በኮሚሽኑ የተመደቡ አንዳንድ "ባለሙያዎች" በምሁርነት ስም አድልዎና ተገቢ ያልሆኑ ሀሳቦችን ሲያራምዱ እንደነበር በመግለጽ ቅሬታውን አቅርቧል።
የተወሰኑ አስተባባሪዎች ደግሞ የፓርቲው ተወካዮችን እና ሌሎች ተሳታፊዎች ያሏቸውን "መሠረታዊ አቋሞችና ሀሳቦች እንዳያቀርቡ ደጋግመው ዕድል ማንሳታቸውን በመግለጽ፣ "በስልታዊ መንገድ አፈና ሲፈጽሙ" መቆየታቸውን ገልጿል።
አብን ያቀረባቸውን አቤቱታዎች ተከትሎ ኮሚሽኑ ጥሰት የፈጸሙ የተወሰኑ አካላትን ለይቶ ከኃላፊነት ማንሳቱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ይህ እርምጃ ሙሉ አይደለም ያለው ፓርቲው "በተለይም የሁለቱ ኮሚሽነሮችና የጥቂት አስተባባሪዎች አሉታዊ ጣልቃ ገብነት" መቀጠሉን እንዲሁም "የመንግሥት አካላት አሠራር ሙሉ በሙሉ አለመታረሙ" ቅሬታ ፈጥሮብናል ብሏል።
ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ አወዛጋቢ ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እና በውጭ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን አሰባስቦ ላለፉት አምስት ሳምንታት ውይይት እያደረገ ይገኛል።
ኮሚሽኑ በለያቸው ስምንት ዋና ዋና የምክክር አጀንዳዎች ላይ ከሐምሌ 8፣ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ምክክር እያደረገ ቢሆንም የአዲስ አበባ ጉዳይ ካላግባቡ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።
ኮሚሽኑ ሰኞ ዕለት ለአብን ቅሬታ በሰጠው ምላሽ ላይ ባለው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ሂደቱን "በነፃነት፣ በገለልተኝነት፣ በአካታችነት እና በአሳታፊነት ለማስኬድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ" እንደሚገኝ አስታውቋል።
አክሎም አብንም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀሪው የምክክር ሂደት ላይ በንቃት እንዲሳተፉና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ እንዲተባበሩ ጠይቋል።
አብን በበኩሉ አገራዊ ምክክሩ "ከግለሰቦችና ከገዥው አካል ወገንተኝነትና ጣልቃ ገብነት" ነፃ ሆኖ እንዲቀጥልና በውጤት እንዲጠናቀቅ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ጠንከር ያሉ ምክክሮች መደረጋቸውን እና የፌደራል ከተሞች ጉዳይ ላይ "ጠንከር ያሉ አቋሞች" መታየታቸውን ለብሔራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ጠቅሰው ነበር።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም በምክክሩ ሂደት "ከውጭም ሆነ ከውስጥ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ" አለመደረጉን ገልጸው፣ ይህንንም "ሥራችንን የፈተሹ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም የውጭ ሰዎችም አይተውታል"ብለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ ሰኞ ዕለት ስለአጠቃላይ ሂደቱ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ቀናት ስምንቱ የአጀንዳ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 16 ተመካካሪዎችን መርጠው ከየቡድኑ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን ለማጣጣም ሲሰሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
ይህ የማጣጣም ሥራ በምክረ ሀሳቦች ውስጥ ተቃርኖ እና ድግግሞሽን በማስቀረት ወጥ በሆነ መንገድ እንዲቀርቡ የሚያስችል ነው፡፡
ስምንቱ ቡድኖች በሚቀርቡላቸው ምክረ ሀሳቦች ላይ ያላቸውን ግብዓቶች ሰጥተው ረቡዕ እንደሚጸድቅም ጨምረው አስታውቀዋል።















