ሩሲያ ውስጥ ያለ ግድብ ተደርምሶ 15 ማዕድን አውጪዎች ሞቱ

ታትሟል

ሩሲያ ውስጥ በምትገኘው ሳይቤሪያ በሚገኝ የወርቅ ማዕድን ማውጫ አካባቢ ያለ ግድብ ተደርምሶ ቢያንስ 15 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 13 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም ተባለ።

ክራስኖያርክ በተባለው ክልል ውስጥ በሴይባ ወንዝ ላይ የተገነባው ግድብ ዛሬ (ቅዳሜ) በአካባቢው የጣለን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በመደርመሱ የማዕድን ማውጫው ሠራተኞች የሚኖሩባቸውን ቤቶች በማጥለቅለቁ ነው አደጋው የደረሰው።

የሩሲያ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ከሞቱትና እየተፈለጉ ካሉት ሰዎች በተጨማሪ 14 የማዕድን ማውጫው ሠራተኞች ለህክምና ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ከመካከላቸውም ሦስቱ የከፋ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

ግድቡ የግንባታ ደንቦችን አላከበረም በመባሉ የወንጀል ምርመራ እየተደረገ ነው።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአደጋውን ምክንያት ለማወቅ ለሚደረገው ምርመራ ባለስልጣኖቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ኢንትርፋክስ የተባለው የዜና ወኪል እንደዘገበው የማዕድን ማውጫው ሠራተኞች የሚኖሩባቸው በርካታ ትናንሽ ቤቶች በከባዱ የጎርፍ ውሃ ተጠርገው ተወስደዋል።

የማዕድን ማውጫው የሚገኘው ከሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ከ4ሺህ ኪሎ ሜትሮች በስተ ምሥራቅ ርቆ በሚገኝ ስፍራ መሆኑም ተነግሯል።

አደጋው ከደረሰ በኋላ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት የተሰማሩ ሲሆን በተጨማሪም ደብዛቸው የጠፋውን ሰዎችንም በመፈለግ ላይ ናቸው።

የሴይባ ወንዝና በአካባቢው ያለው የጎርፍ ውሃ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ከማዕድን ማውጫ አቅራቢያ በሚገኝ መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከአካባቢው እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።