የቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች ችግር ከ3 ዓመታት በፊት ተደርሶበት እንደነበር ይፋ ሆነ

ታትሟል

ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ወድቆ ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት በሆነው የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ስላለው የበረራ ደህንነት መቆጣጠሪያ ሥርዓት ችግር በተመለከተ ሠራተኞች መልዕክት መለዋወጣቸው ይፋ ሆነ።

ከሦስት ዓመት በፊት አውሮፕላኑ ለበረራ ብቁ ስለመሆኑ ማረጋገጫ በተሰጠበት ወቅት ነው የቦይንግ ሠራተኞች የአውሮፕላኑን የበረራ ደህንነት የሚቆጣጠረውን አውቶማቲክ ሥርዓትን በተመለከተ አጭር የጽሁፍ መልዕክት መለዋወጣቸው የተነገረው።

ለአሜሪካ ሕግ አውጪዎች በቀረበ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፤ አንድ አብራሪ በሙከራ በረራ ወቅት ያልተጠበቀ ችግር ገጥሞት እንደነበረ በጽሁፍ አስፍሯል።

አብራሪው ሳያውቀው የአውሮፕላኑን ደህንነት ለሚቆጣጠሩት ባለሙያዎች መዋሸቱን ገልጿል።

ይህን አብራሪው አስተላልፎታል የተባለውን መልዕክት ተከትሎ ሌላ የቦይንግ ሠራተኛ በጽሁፍ ባሰፈረው ምላሽ "ውሸት አልነበረም፤ ስለጉዳዩ ማንም አልነገረንም ነበር" ብሏል።

ትናንት አርብ ይህ ሪፖርት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ቦይንግ በአክስዮን ገበያ ላይ ያለው ዋጋ ከአምስት በመቶ በላይ መውረዱ ተገልጿል።

ይህ የአውሮፕላኑ የደህንነት መቆጣጠሪያ ሥርዓት ባጋጠመው ችግር ሳቢያ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢንዶኔዢያ አውሮፕላኖች ላይ አደጋን አስከትሎ ለ346 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር አሁን ይፋ ስለተደረገውና በሰራተኞች መካከል የተደረገው የመልዕክት ልውውጥ መረጃ "እንዳሳሰበው" ገልጿል።

ጨምሮም ቦይንግ ስለምን ይህንን መረጃ የያዘውን ሰነድ ቀድሞ እንዳላቀረበ "በአስቸኳይ" ማብራሪያ እንዲሰጥ አዟል።

ቦይንግ ይህንን ሰነድ ያቀረበው አደጋውን በተመለከተ ለህግ አውጪዎች በዚህ ወር ውስጥ ከሚሰጠው ማብራሪያ ቀደሞ ነው።

የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዴኒስ ሙሊንበርግ ከህግ አውጪዎቹ ፊት ቀርበው ምስክርነት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሙሊንበርግ ምንም እንኳን በኃላፊነታቸው የሚቆዩ ቢሆንም በቅርቡ ከቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርነታቸው ተነስተዋል።

ቦይንግ እንደሚለው ሁለት አደጋዎች ካጋጠሙት በኋላ በዓለም ዙሪያ ከበረራ ውጪ እንዲሆን የተደረገውን 737 ማክስ ላይ ለሚደረገው ምርመራ ትብብር እያደረገ ነው።

ኩባንያው በቅርቡ እንዳሳወቀው የሚያመርታቸውን አውሮፕላኖችና አገልግሎታቸውን በተመለከተ ምርትና ሥራቸውን በበላይነት የሚቆጣጠር ቋሚ ኮሚቴ ማቋቋሙን ገልጾ ነበር።

በኢትዮጵያውን በኢንዶኔዢያ የአውሮፕላን አደጋዎች ላይ ምርመራ ያደረጉት ባለሙያዎች ለአደጋዎቹ ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል በሚል ትኩረት ያደረጉት አውሮፕላኑ በቀላሉ እንዲበር ያደርገዋል ተብሎ የተሰራለት የበረራ ደህንት መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ላይ ነው።

ምርመራዎች እንዳመለከቱት ይህ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት በአግባቡ ካለመስራቱ በተጨማሪ አውሮፕላኖቹን ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ አደጋዎቹን አስከትለዋል።

ቦይንግ በበኩሉ አደጋዎቹ ያጋጠሙት በመቆጣጣሪያ ሥርዓቱ በተጫነው የተሳሳተ መረጃ የተነሳ መሆኑን ጠቅሶ ይህንንም ለማስተካከል ክለሳ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ቦይንግ አገኘሁት ያለው ይህ አዲስ የመልዕክት ልውውጥ ከሦስት ዓመታት በፊት የተደረገ ሲሆን፤ መረጃውን ያሰፈረው አብራሪም በአሁኑ ጊዜ በኩባንያው ውስጥ እንደማይሰራ ተገልጿል።