በዩክሬን ግድብ ላይ የደረሰው ጉዳት በለም መሬቶች ላይ የረጅም ጊዜ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ተባለ

ታትሟል

በዩክሬን በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት ቤታቸው ለተጎዳባቸውና ለተፈናቀሉ ሰዎች በአስገራሚ ሁኔታ በቂ አስቸኳይ እርዳታ ቀርቦላቸዋል።

ሆኖም በአገሪቱ እጅግ ለም ከሆኑ አካባቢዎች ከሆኑ በአንዱ የተከሰተው ይህ ጎርፍ በግብርና ላይ የከፋ የረጅም ገዜ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የዩክሬን ባለሰልጣናት እያሳሰቡ ነው።

የግብርና ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው ትንበያ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙ የእርሻ ቦታዎች በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ “ወደ በረሃነት” ሊቀቀየሩ ይችላሉ ብሏል። የዚህም መነሻ ካኮቫካ የተባለው የውሃ ማቆሪያ ላይ የተመሰረተው ወሳኝ የመስኖ ተፋሰስ ስራ በማቆሙ እንደሆነ አመላክቷል።

የውሃ ማቆሪያው በፍጥነት እየተሟጠጠ ሲሆን በውስጡ ያለው ውሃ ዲንፕሮ በተሰኘው ወንዝ አማካኝነት ወደ ጥቁር ባህር እየተጓዘ ነው።

በዩክሬን ያለው ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት 31 የመስኖ ተፋሰሶች ለ584 ሺህ ሄክታር መሬት ውሃ ያቀርቡ እንደነበር ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የዩክሬን ግብርና ተቀዳሚ ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ታራስ ቫይስቶስኪይ ጉዳት የደረሰበት ግድብ ለመስኖ ብቸኛው የውሃ ምንጭ እንደነበር ገልጸዋል።

ምክትል ሚኒስትሩ የግድቡ ውሃ የመሳቢያና የማሰራጭያ ጣቢያው መውደሙን የገለጹ ሲሆን “አርሶ አደሮች ከመስመሮቹ ውሃ ማግኘት ካላባቸው እንደ አዲስ አንድ ተብሎ መገንባት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

የኬርሶን ግዛት ዩክሬን ካሏት ለምና ምርታማ አከባቢዎች አንዱ ነው፝”

አከባቢው ከሚታወቅበት የሃባብ ምርት በተጨማሪ በዲፕሮ ወንዝ አማካኝነት በሁሉም አቅጣጫ መሬቱ የተለዩ የእህል ዘሮች፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና የሱፍ አበባን ያበቅላል። የእንስሳት እርባታም ተጽዕኖ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችልም ተገልጿል።

ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የጠቀለለችውን ክሪሚያን ጨምሮ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ያሉት የዩክሬን ግዛቶች በጎርፉ ምክንያት ከዚህም የከፋ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ተብሏል።

ዩክሬን ከዚህ ሁሉ ቀወስ ጀርባ ሩሲያ እንዳለች ብትገልጽም ሞስኮ ግን ከግድቡ መደርመስ ጀርባ እጇ እንደሌለበት አስተባብላለች።

ሩሲያ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሁሉም ዘርፎች ስትሰጣቸው የቆየችው ከእውነት የራቁ መረጃዎች ምክንያት የግድቡን ከአገልግሎት ውጪ መሆን በተመለከተ የሰጠችው አስተያየት በጥርጣሬ እንዲታይ አደርጎታል።

ባለስልጣናት ጉዳት በደረሰበት የግድቡ ክፍል በኩል ያለውን የውሃ ፍሰት መጠን ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ነው።

ግድቡን መልሶ ለመጠገን ወይም መልሶ ከመጀመሪያ ጀምሮ ለመገንባት እስከ 5 ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ምክትል ሚኒስትሩ የተናገሩ ሲሆን በዚህ ምክንያት “በአምስት ዓመት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ስለምናጣ ከጠቅላላ ዘርፉ የምናጣውን ስናሰላው 7 ቢሊዮን ዶላር” ይሆናል ብለዋል።

ሌላኛው የግድቡ ጉዳት ያስከተለው ችግር ደግሞ ከአየር ብክለት ጋር የተያያዘ ነው።

ግድቡ በሚወድቅብት ጊዜ ለከባቢ አየር ጸር የሆኑና ከፍተኛ መጠን ያላቸው ኬሚካሎች ውሃማ አካላትን ተቀላቅለዋል።

በአከባቢው ላይ የአየር ብክለት መኖሩን ባለሙያዎች የተናገሩ ሲሆን ያለውን ተጽዕኖ ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት ሳምንት ይወስዳል ብለዋል።