ሳይንቲስቶች ራሷን በራሷ ያስረገዘች አዞ አገኙ

ታትሟል

ሳይንቲስቶች የመጀመሪያ የተባለችውን ራሷን በራሷ ያስረገዘች አዞ ማግኘታቸውን አስታወቁ።

አዞዋ የተገኘችውም በኮስታሪካ በሚገኝ መካነ እንስሳ ውስጥ ነው።

ጽንሱ (ጫጩቱ) 99.9 በመቶም በዘረ መል ከራሷ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ነው ተብሏል።

እርግዝናው “በድንግልና መውለድ” እየተባለ የሚጠራ ክስተት ሲሆን በወፎች፣ በአሳ እና በሌሎች ተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች ላይ የታየ ሲሆን በአዞ ላይ ሲከሰት የመጀመሪያው ነው።

ሳይንቲስቶች ይህ ባህርይ በዝግመተ ለውጥ ውስጥ ከነበረ ጥንታዊ አዞ የተወረሰ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ሰጥተው በዚህም ዳይኖሰሮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስረገዝና የመራባት ችሎታም ሊኖራቸው እንደሚችልም ተጠቁሟል።

ይህ ጥናትም በሮያል ሶሳይቲ ስነ ህይወት ጆርናል ላይም ታትሟል።

እንቁላሉ በአውሮፓውያኑ 2018 ፓርክ ሬፕቲላኒያ ውስጥ በተሰኘው መካነ እንስሳ በነበረች 18 ዓመት እድሜ ባላት አሜሪካዊት አዞ ነበር የተጣለው።

በእንቁላሉ ውስጥ የነበረው ጽንስ ሙሉ በሙሉ የአዞነት ቅርጽ ቢኖረውም በህይወት ግን አለመኖሩ ተገልጿል።

እንቁላሉን የጣለችው አዞ የተገኘችው በሁለት ዓመቷ ሲሆን ከሌሎች አዞዎች ተለይታም ነው እስካሁን የኖረችው።

በዚህም ምክንያት የፓርኩ የሳይንስ ቡድን የቤልፋስት ተወላጁን ዶ/ር ዋረን ቡዝን አነጋግሯል። ዶ/ር ዋረን በሳይንስ ፓርቴኖጀነሲስ በመባል የሚታወቀውን “በድንግልና መውለድ” ለ11 ዓመታት ሲያጠኑም ቆይተዋል።

ባለሙያው ጽንሱን ከመረመሩ በኋላ ከ99.9 በመቶ በላይ ከእናቱ ጋር በዘረ መል ደረጃ ፍጹም ተመሳሳይ እንደሆነና አባት እንደሌለውም አረጋግጠዋል።

ግኝቱ እንዳላስገረማቸውም ተናግረዋል።

“በሻርኮች፣ ወፎች፣ እባቦች እና እንሽላሊቶች ላይ ይታያል። ይህ ክስተት በሚያስደንቅ ሁኔታ የተለመደ እና የተስፋፋም ነው” ብለዋል።

በአዞዎች ላይ የፓርታኖጄነሲስ ሁኔታ ከዚህ ቀደምም ያልታየበት ምክንያት ሰዎች ይህንን በአዞዎች ላይ ባለመፈለጋቸው እንደሆነም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

“ሰዎች እባቦችን እንደ ቤት እንስሶች ሲያስቀምጡ በራሳቸው መራባታቸውን (ፓርቴኖጀነሲስ) ሪፖርቶች ጨምሮ አይተናል። አዞዎች ግን እንደ ቤት እንስሶች ስለማይታዩ ይኼንን አልተመለከትንም “ ብለዋል።

በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ፓርቴኖጀነሲስ የሚከሰተው በመጥፋት ላይ ባለ ዝርያና ቁጥራቸውም ሲቀንስ ነው።