ፑቲን በዩክሬን ጦርነት ዙርያ ከከፍተኛ የጦር ጄኔራሎቻቸው ጋር መከሩ  

ታትሟል

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ከከፍተኛ የጦር መኮንኖቻቸው ጋር ተወያዩ።  

ውይይቱ የተደረገው ከትናንት በስቲያ ዐርብ ዕለት በልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ዕዝ ዋና ማዘዣ ቅጥር ግቢ ነው። 

ፑቲን ከጄኔራሎቻቸው ጋር የመከሩት በዋናነት የዩክሬንን ጦርነት ቀጣይ አቅጣጫን በተመለከተ ነው። 

ከሰሞኑ ሩሲያ በዩክሬን የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ላይ አዲስና መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ከፍታለች። 

ይህ ውይይት እየተደረገ ያለውም ጥቃቱ ተጠናክሮ በቀጠለበት በዚህ ጊዜ ነው። 

የሩሲያን የአየር ጥቃት ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናዊያን በጨለማ ተውጠዋል።  

ሌሎች ሚሊዮኖች ደግሞ ያለ ማሞቅያ የውርጩን ወቅት በከባድ ችግር እያለፉት ይገኛሉ። 

በትናንቱ ስብሰባ ፑቲን በመከላከያ ሚኒስትራቸው ሰርጌይ ሾይጉ እና በምድር ጦር አዛዡ ቫልሪ ገላሲሞቭ ግራና ቀኝ ታጅበው ታይተዋል። 

“የጦር መኮንኖቻችንን በእያንዳንዱ ዘመቻ ዙርያ ያላቸውን ዕቅድ እናዳምጣለን፤ በአጭርና መካከለኛ ጊዜ ጦርነቱን እንዴት እናስኪደው በሚለው ዙርያ ያላችሁን ዕቅድ አቅርቡልኝ” ብለው ፕሬዝዳንት ፑቲን ሲናገሩ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ታይተዋል። 

የምድር ጦሩ አዛዥ ጄኔራል ገራሲሞቭ ከፑቲን ጎን ተቀምጠው መታየታቸው ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል በሚል የተነዛውን ወሬ ሐሰተኛነት ያረጋገጠ ነበር። 

የ67 ዓመቱ ጄኔራል ገራሲሞቭ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‘ጥንቃቄ ያበዛሉ’ በሚል በወታደር አዋቂዎች ክፉኛ ሲብጠለጠሉ ነበር። 

የአየር ኃይሉ ጄኔራል ሰርጌይ ሱሩቪኪንም በዚህ ስብሰባ ተገኝተው ነበር። 

የዩክሬን ወታደሮች ኬርሶን ከተማን መልሰው ከእጃቸው ማስገባታቸውን ተከትሎ በርካታ አካባቢዎች መቆጣጠር ችለዋል። 

ይህን ተከትሎ ሩሲያ እየወሰደቻቸው ያሉትን የአጸፋ የአየር ጥቃቶች ግን የዩክሬን ኃይሎች መቋቋም አልቻሉም። 

በዚህም ምክንያት ይመስላል አሜሪካ ለዩክሬን ከሰሞኑ ፓትሪዮት የተሰኙትን የላቁ የአየር መቃወሚያዎችን ለመስጠት ቃል የገባችው። 

ሩሲያ በአየር ኃይል ብልጫ እያገኘች ብትመጣም በምድር ጦር አልተሳካላትም።

የሞስኮ ኃይል በተለይ በምሥራቅ ዩክሬን ከዕለት ዕለት እየተፈረካከሰ በመምጣቱ የሩሲያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የክሬምሊን ደጋፊ በሆኑ ተንታኞችና ሚዲያዎቻቸው ዘንድ ክፉኛ እንዲብጠለጠሉ አድርጓቸዋል። 

የዩክሬን አንድ ከፍተኛ የጦር ጄኔራል የዚህ ስብሰባ ዓላማ ሩሲያ በ2023 ዓ/ም መጀመርያ ላይ ልትከፍት ላሰበችው መጠነ ሰፊ ማጥቃት ዝርዝር ዕቅድ መንደፍ ነው ብለዋል።

እኚህ የዩክሬን ከፍተኛ የጦር ጄኔራል እንደሚሉት ፑቲን ለአዲሱ ዓመት አዲሱ ወረራ 200ሺህ ሠራዊት አሰናድተዋል። 

ጄኔራሉ ይህ የአዲሱ ዓመት ጥቃት ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ አቅጣጫ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።  

የጥቃቱ መነሻም ቤላሩስ ትሆናለች ብለዋል። 

ባለፈው የካቲት ወር የሩሲያ ኃይል ጥቃት ሲከፍት በቅድሚያ ለመያዝ የሞከረው ዋና ከተማዋን ኪየቭን ነበር።  

ሆኖም ይህ ዘመቻ ስኬታማ ሳይሆን መቅረቱ ይታወሳል። 

በዚያን ጊዜም ቢሆን የሩሲያ ኃይል የተነሳው ከጎረቤት ቤላሩሰ ድንበር ነበር። 

የቤላሩስ መሪ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ በተደጋጋሚ ጦራቸው በዚህ ወረራ እንዳልተሳተፈ ቢናገሩም አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ግን የሩሲያ ጦር ከቤላሩስ መከላከያ ጋር ልምልድ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። 

ቪላድሚር ፑቲን የቤላሩሱን አቻቸውን ነገ ሰኞ በሚንስክ ይጎበኟቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። 

የዩክሬን ጄኔራል በአዲሱ ዓመት ሩሲያ አዲስ ጥቃት ትከፍታለች የሚለውን መላምት የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት “አይመስለንም” ሲል ተቃርኖታል። 

አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር ደኅንነት ኃላፊ እንደተናገሩት “ሩሲያ ከዚህ ወዲህ መጠነ ሰፊ ዘመቻ የመክፈት አቅሟ ተሟጧል። ”