ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቀሳውስት እና ጳጳሳት ለመሆን እየታገሉ ያሉት ሴቶች
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለውጥ እንድታካሂድ እየተጠየቀች ነው።
በቤተ ክርስቲያኗ ያሉ ሴት አገልጋዮች የቅስና፣ የጵጵስና ማዕረግ ሊሰጠን ይገባል፤ ቤተ ክርስቲያኗ ቀኖናዋን ልትቀይር ይገባል በማለት እየሞገቱ ነው።
የቤተ ክርስቲያኗን አሻፈረኝ ማለት ያልተቀበሉ ሴቶች ደግሞ የቅስናና የጵጵስና ማዕረግ በራሳቸው እየተቀበሉ ይገኛሉ።
አን ትሮፒአኖ በዓለም ዙሪያ ባሉ የካቶሊክ ቄሶች የሚለበሰውን ልብሰ ክህኖ እየተኮሰች ነው። በግድግዳዋ ላይ ባለው የቀን መቁጠሪያ ላይ በደማቅ ቀለም በካህንነት የምትቀባበትን ቀን ጎላ ብሎ ይታያል።
አን የቅስና ማዕረግ መቀበል ጠላት እንደሚገዛላትም ስላወቀች በኒው ሜክሲኮ፣ አልቡከርኪ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን በሚኖረውም የአገልግሎት ሥነ ሥርዓትንም እንዲጠብቁላት የጥበቃ ሠራተኞችን ለመቅጠር በስልክ እየተነጋገረች ነው።
“እኛ ቅስናን መቀበላችን ከፍተኛ ውጥረት የተሞላበት ነው። ሴቶች ቀሳውስት መሆን ይችላሉ የሚለውን ሃሳብ ለማስተናገድ የማይችሉ በርካቶች ናቸው” ትላለች አን።
አን የሚያሳስባት አካላዊ ትንኮሳ ብቻ አይደለም። የካቶሊክ ቄስ መሆን እንደምትፈልግ የሕይወት ጥሪዋን ካካፈለችበት ወቅት ጀምሮ በበይነ መረብ ላይ ዱላ ቀረሽ ትንኮሳዎችን አስተናግዳለች።
አን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀሳውስት ለመሆን ከቆረጡ 200 ሴቶች አንዷ ናት።
እነዚህ ሴቶች የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሴቶች የካህንነት ማዕረግ መቀበል አይችሉም የሚለውን ሕግም ባለመቀበል የራሳቸውን እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በዚህም የቤተ ክርስቲያኗን ሕግ ተላልፈው በራሳቸው ቅስናን እየተቀበሉ ይገኛሉ።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሴቶች ቅስና አይፈቀድላቸውም ብቻ ሳይሆን፣ በቀኖናዋ መሠረት እንደ ከባድ ወንጀልም ነው የምትመለከተው።
ለዚህም ቅጣት ያለው ሲሆን ይህም ተወግዘው ከየትኛውም የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ይደረጋሉ። ይህም ማለት እነዚህ ቅስናን የተቀበሉ ሴቶች መቁረብን ጨምሮ፣ በቤተ ክርስቲያኗ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዳይቀበሩም ይሆናል።
“ለረዥም ዓመታት ቄስ መሆን እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያኗ ተወግዤ እወጣለሁ በሚል ወደ ጎን ገሸሽ አደረግኩት” ትላለች።
ሆኖም በየቀኑ ቅዳሴን ጨምሮ እያንዳንዷን የቤተ ክርስቲያኗን አገልግሎት በመከታተልና በማገልገልም ነው ሕይወቷን ያሳለፈችው። ሕይወቷን ለቤተ ክርስቲያኗ የሰጠች ናት አና።
አና አጥባቂ ካቶሊክ ናት ከዚህ ቀደም የሮክ የሙዚቃ ባንድን ማስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችንም አከናውናለች።
ነገር ግን በአንድ ወቅት የክህነት ጥሪ እንደደረሳት ትናገራለች “በተደጋጋሚም ይህንን ቃል እሰማ ነበር። አንቺ የእኔ ካህን ነሽ፣ ካህን ነሽ፣ ካህን እንድትሆኝ አፈልጋለሁ” የሚልም ነበር።
በቤተ ክርስቲያኗ ለሴቶች ቅስና የማይታሰብ በመሆኑም ያላት አማራጭ በመነኩሴነት ወይም በአገረ ስብከት አስተዋፅኦ ማድረግም ነበር። ወይም ወደ ሌላ የክርስትና እምነት በመሄድ ቅስናን በዚያ መቀበልና የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን እርግፍ አድርጎ መተው።
ከዓመታት በኋላ ግን የቫቲካን የማውገዝ ሕግ ቅስናዬን አይገድበውም የሚለው ውሳኔ ላይ ደረሰች። መወገዙንም በጸጋ እንደምትቀበለው ራሷን አሳመነች። አና ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ቅስናን የመረጡ ሴቶች በቤተ ክርስቲያኗ “የፆተኝነት ሕግ” ላይ የከፈቱት ዘመቻ እንደሆነ ነው እያዩት ያሉት።
ተሃድሶ ይሁዲን ጨምሮ ፕሮቴስታንት እና ሌሎች እምነቶች ለሴቶች የቅስና ማዕረግ ለመስጠት ክፍት ናቸው።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸው 12 ሃዋርያት ወንዶች መሆናቸውን በመግለጽ፣ የዕምነት ተቋሟ የክርስቶስ አምሳያ ነው በማለት ክልከላዋን አፅንታለች።
“በቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ መሰረትና በተግቧሯ ሴቶች የበታች መሆናቸውን ታሳያለች። ሴቶች፣ ህፃናት እና ወንዶች ይህንን እሳቤ ነው የሚማሩት። በዓለም ላይ ሴቶች የበታች ናቸው በሚል ጽንሰ ሃሳብ ነው ሕይወታቸውን የሚገፉት” ትላለች አና።
የቅስና ሥነ ሥርዓት በመርከብ ላይ
የሴቶች የቅስና እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተሰሚነት ያገኘው በአውሮፓውያኑ 2002 ነው። ሰባት ሴቶችን የያዘ ቡድን በዳኒዩብ ወንዝ በሚገኝ ዓለም አቀፍ ውሃ ላይ የቅስናን ማዕረግ ተቀበሉ። ከቤተ ክርስቲያኗ ውጪ ቀሳውስት የሆኑት እነዚህ ሴቶች ይህን ስፍራ የመረጡት ከትኛውም አገር ጋር ግጭት ውስጥ ላለመግባት ነው።
ሆኖም በ1970ዎቹ በቼኮዝሎቫኪያ የኮሚዩኒስት አገዛዝ ወቅት በአንድ የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ በተመራ ምስጢራዊ ቅስና እንደ ሉድሚላ ጃቫሮቫ ያሉ ሴቶች ቄስ ሆነዋል ተብሏል።
የሴቶች የቅስና እንቅስቃሴ በአብዛኛው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ቢሆንም በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ተስፋፍቷል።
ከ1.3 ቢሊዮን የዓለም ካቶሊክ ምዕመናን ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው ምዕመናን የእምነቱ ተከታይ በሆነባት ላቲን አሜሪካ፣ ኮሎምቢያዊቷ ኦልጋ ሉሲያ አልቫሬዝ በላቲን አሜሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ቄስ ሆኑ።
በአውሮፓውያኑ 2010 የነበረው የቅስና አሰጣጥ ምስጢራዊ ቢሆንም ከቤተ ክርስቲያኗ አንዳንድ አካላት ድጋፍ እንዳገኘች ይናገራሉ “አንድ ጳጳስ ነበሩ። በቫቲካን ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ስማቸውን አንገልጸውም። ድጋፋቸውን ሰጥተውናል” ብለዋል።
“በምኖርበት ከተማ ወግ አጥባቂ ማኅበረሰብ በመሆኑም ድንገት ሰዎች ይሰድቡኛል ወይም በአገልግሎት ወቅት የሆነ ነገር ይወረውሩብኛል ብዬ ፈርቼ ነበር” በማለት የነበረውን ያወሳሉ።
“ሆኖም ከበርካቶች ያገኘሁት ድጋፍ በጣም የሚያስደንቅ ነው። ይህ ሁኔታም በተልዕኮዬ እንድጠናከል አድርጎኛል” ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ቫቲካን እውቅና በማትሰጠው የሮማ ካቶሊክ ሴት ካህናት ማኅበር ጳጳስ ለመሆን በቅተዋል።
አልቫሬዝ በጣም አጥባቂ ከሆነ የካቶሊክ ቤተሰብ ቢወለዱም መነኩሲት ከሆኑት እናቷም ድጋፍ አግኝተዋል። ቄስ የሆነው ወንድማቸውም ጽዋ በስጦታ መልክ በመስጠት ድጋፉን ሰጥቷቸዋል።
አልቫሬዝ በቅዱሳን መጻህፍት ውስጥ ሴቶችን ከክህነት የሚያግድ ምንም ነገር እንደሌለ አጥብቀው ይከራከራሉ።
“ይህ የሰው ሕግ፣ የቤተ ክርስቲያን ህግ ነው። እናም ኢ-ፍትሃዊ በመሆኑ መሻር አለበት” በማለት ይሞግታል።
ይህንንም ሃሳብ ቫቲካን ሕጓን እንድትቀይርና ለሴቶች የቅስና እና የጵጵስና ማዕረግ እንድትሰጥ ውይይቶችን እና ሰልፎችን የሚያካሂደው የሴቶች የቅስና ጉባኤም የሚደግፈው ነው።
የጳጳሱ የተሽከርካሪ አጀብ በከተማዋ ውስጥ ሲያልፍ መንገድ ላይ ከመተኛት ጀምሮ፣ ሮዝ ጭስ በማውጣት ለየት ያሉ ተቃውሞችን የሚያካሂዱት እነዚህ ሴቶች በቫቲካን ፖሊስ በተደጋጋሚ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ቫቲካን “በፆተኝነት ሕጓ ሃጥያት እየሰራች ነው” የሚሉት እነዚህ ሴቶች፣ ቤተ ክርስቲያኗ ሕጓን ካልቀየረች ይህንን ኢ-ፍትሃዊ ሕግ ከመጣስ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
“የተዘጋው የቅስና በር”
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት ሴቶቹ እያደረጉት ያለው የቅስናም ሆነ የጵጵስና መቀባት ጥያቄ እንደ ሕገወጥ ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት እንደሌላቸው ነው የምታያቸው።
የዳኒዩብ የመርከብ የቅስና ሥርዓት ይፋ ከሆነ በኋላ ብፁዕ ካርዲናል ጆሴፍ ራትዚንገር፣ በኋላም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት “ሴቶቹ ምንም አይነት የመጸጸት ምልክት ስላላሳዩ በሰሩት ከባድ ጥፋት ከቤተ ክርስቲያኗ ተወግዘው እንዲወጡ ተወስኖባቸዋል” ብለዋል።
ፖፕ ፍራንሲስም ሴት ቄስ አትሆንም አሉ። በአውሮፓውያኑ 2016 ቤተ ክርስቲያኗ ይህንን ሕግ የመለወጥ ሁኔታ ዕድል ሊኖር ይችል ይሆን ወይ? ተብለው የተጠየቁት ፖፑ “የዚህ ጥያቄ በሩ የተዘጋ ነው” ሲሉ በአውሮፓውያኑ 1994 የወጣ ሰነድን በመጥቀስ አፅንኦት በመስጠት ምላሽ ሰጥተዋል።
በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥልጣኑን የተቆጣጠሩት ወንዶች ቢሆኑም ባለፈው ዓመት በጳጳሳት ሲኖዶስ ውስጥ ከፍተኛ የተባለውን የፀሐፊነት ስፍራ ለመነኩሴዋ ናታሪ ቤኳዋርት ተሰጥቷል። ይህ የጳጳሳት ሲኖዶስ ጳጳሱን የሚያማክር አካል ነው።
በአሁኑ ወቅት ሴቶች ቅስናን የመቀበል ጥያቄ ለቤተ ክርስቲያኗ የተዘጋ ጥያቄ መሆኑን ነው መነኩሴዋ የሚናገሩት።
“ለቅስና ተጠርቻለሁ የሚል ስሜት ሳይሆን ሁልጊዜም መቅደም ያለበት ቤተ ክርስቲያኗ ስትጠራችሁና እውቅና ስትሰጣችሁ ነው። የግል ስሜት በቂ አይደለም” ብለዋል የፈረንሳይ ዜጋ የሆኑት መነኩሴ
በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ቁልፍ ሹመት የተሰጣቸው መነኩሴ በቫቲካን ውስጥ የመምረጥ መብት ያላቸው የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው።
ሴቶች በቤተ ክርስቲያኗ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ጥረቶች አሉ የሚሉት መነኩሴ ሆኖም ቅስና ገና ነው ብለዋል።
“ስለቤተክርስቲያን ያለንን ዕይታ ማስፋት ያለብን ይመስለኛል። ሴቶች ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉባቸው በርካታ መንገዶች አሉ” በማለት ቤኳዋርት ያስረዳሉ።
ነገር ግን ለውጥ መቼም ቢሆን ቀላል እንዳልሆነ እና ሁልጊዜ “በፍርሃት እና በተቃውሞ” የተሸበበ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለሴቶቹ የተለየ መንገድ
ፀጥታ በተሞላበት ካቴድራል አን ትሮፔኖ ቅስናዋን ለመቀበል ወደ ጳጳሷ እየተጠጋች እና በስሜት ተሞልታ “ይኸው ዝግጁ ነኝ፤ ብላ ተናገረች።”
ይህችን ቀን ለማየት 14 ዓመት ጠብቃለች። የቅስናው የምትቀበልበት ሥነ ሥርዓት ለወንድ የካቶሊክ ቄሶች ከሚደረገው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ነው የተካሄደው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የቅስናውን ሥርዓት የመሩት ጳጳስ ብሪጅት ሜሪ ሚሃን የአና ትሮፔናን እጆች አንስተው እያጨበጨበ ወደነበረው ጉባኤ አቀረቧት። ይህች ዕለት ለአን ከፍተኛ እና የተቀደሰች ዕለት ሆነች።
አና ትሮፔና የሥልጣን ተዋረድ በማይታይበት፣ የተለያዩ ቡድኖችን የሚያቅፍ ቤተ ክርስቲያን ቅርንጫፍ አካል በመሆኗም ኩራት ይሰማታል።
“ተፋታችሁ አልተፋታችሁ ምንም ለውጥ አያመጣም። ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪም ብትሆኑ ሁላችሁም ቦታ አላችሁ” ብለዋል።
የአን የቅስና ሹመት የተሰጣት በአሜሪካ፣ ኒው ሜክሲኮ፣ በአልቡርኪ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ነው።
ጳጳስ አልቫሬዝም ቢሆኑ የካቶሊክ ሴቶች ቅስና ማዕረግ ከወንድ ቄሶች ወሲባዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የተሸረሸረውንም እምነት በተወሰነ መልኩ ያስተካክለዋል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
“እንዴት በምድር ላይ የእግዚአብሔር ብቸኛ ተወካዮች ናቸው ይላሉ? ምንም አያፍሩም" ሲሉም የካቶሊክ ቄሶች በዓለም ላይ ስለፈጸሙት መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃቶች ይናገራሉ።
ፖፕ ፍራንሲስ በሃይማኖት አባቶች በተፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችን ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ "የከፉ ወንጀሎችን ለመደበቅ ያደረገችውን ጥረት” አውግዘዋል።
ጳጳስ አልቫሬዝ የሴቶች ቅስና ለዚህ መልስ ነው ይላሉ። የ80 ዓመቷ ጳጳስ ቄስ ለመሆን ተስፋ ያደረጉ ታዳጊ ሴቶችን በማማከር ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።
“ታሪክ ራሱን እንዲደግም መፍቀድ የለብንም። ሴቶች የቅስናን ሌላ ገጽታ ማሳየት አለባቸው” ይላሉ።
በላቲን አሜሪካ ካሉ አገራት ውስጥ ከፍተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ባለባት ብራዚል ውስጥ ከአስር የሚጠጉ ስምንት ካቶሊኮች ሴቶች ቅስና ቢሰጣቸው እንደሚደግፉ ተናግረዋል ።
በአውሮፓውያኑ 2014 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በአሜሪካ ከአስር ሰዎች ስድስቱ ይህንን ይደግፋሉ። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ባለባት አፍሪካ የሴቶች ቅስና ጥያቄ ብዙም አላንሰራራም።
አን ትሮፔኖ ለቤተ ክርስቲያኗ የወደፊቱ ዕጣ ፈንታ ሴቶች በእኩልነት መሳተፍ እንዳለባቸው ትናገራለች።
“በቤተክርስቲያኗ እኩል ተሳትፎ እስከሌለ ድረስ ተልእኮዋን መወጣት አትችልም።በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ ነገር የለም” ብላለች።