አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ50 አገራት አመልካቾች ለቪዛ የሚያስይዙትን ገንዘብ በመጨመር ቋሚ ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የበርካታ አገራት ዜጎች ቪዛ ሲያመለክቱ ያስይዙት የነበረውን ገንዘብ ከ15 ሺህ ዶላር ወደ 20 ሺህ ዶላር ከፍ በማድረግ ቋሚ ሊያደርግ ነው።
መሥሪያ ቤቱ ዓርብ ዕለት በገጹ በለጠፈው ማስታወቂያ ላይ እንደገለፀው መርሃ ግብሩ የቢዝነስ እና የቱሪስት (ቢ1 እና ቢ2) ቪዛ አመልካቾች ላይ ተግባራዊ የሚሆን ነው።
ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ አሜሪካ ውስጥ ከቆዩ ገንዘቡ ተመላሽ እንዳይሆን የሚያደርገው ይህ አሠራር ተግባራዊ ይሆንባቸዋል ከተባሉ አብዛኞቹ ከአፍሪካ ከሆኑ 50 አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳ፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያ እና ታንዛኒያ ይገኙበታል።
ይህ በቀናት ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው የተሻሻለው ፕሮግራም፣ ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ የሚቆዩ ጎብኝዎችን ለመከላከል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ መሠረት አመልካቾች እንደ ኤምባሲው ኦፊሰሮች ውሳኔ ለቪዛ እስከ 20 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንዲያስይዙ ሊጠይቁ ይችላሉ።
አሜሪካ ውስጥ ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ዜጎች ባሏቸው አገራት እና የአገር ውስጥ ሰነዶች ላይ የላላ ቁጥጥር በሚያደርጉ አገራት የቪዛ ማስያዣ የሙከራ መርሃ ግብር ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ነበር።
መርሃ ግብሩ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የነበረ ሲሆን የተቀመጠለት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው አዲሱ መመሪያ የወጣው።
በቀናት ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው ይህ አዲሱ የቪዛ ማስያዣ ገንዘብ ፕሮግራም ቋሚ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በተጠናቀቀው የሙከራ መርሃ ግብር መሠረት አመልካቾች ከ5 ሺህ ፣ ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ዶላር ድረስ እንዲያስይዙ ይጠየቁ የነበረ ሲሆን በአዲሱ ፕሮግራም አነስተኛው 5 ሺህ ዶላር ከዝርዝሩ ወጥቶ፣ ከፍተኛው የማስያዣ ገንዘብ ወደ 20 ሺህ ከፍ ተደርጓል።
በአዲሱ መርሃ ግብር ከተካተቱ 50 አገራት መካከል 30ዎቹ የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት እርምጃው የቪዛ ቀናቸው ከበቃ በኋላ የሚቆዩ ሰዎችን ለመቀነስ ያለመ ነው።
ሆኖም የኢምግሬሽን ተሟጋቾች ፕሮግራሙ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ጉዞዎችን ይገድባል በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል።
የመብት ተሟጋቾችም የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጥብቅ የኢሚግሬሽን ሕግ የመናገር ነፃነትን ጨምሮ ሰብዓዊ መብቶችን እየገፈፈ ነው ይላሉ።
በትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ምክንያት የተወሰኑ ጎብኚዎች ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት እየሰረዙ መሆኑም ይሰማል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ማስወጣት እንዲሁም የድንበር ቁጥጥሩን ለማጠናከር በጀት ከፍ የማድረግ እና ወደ አገሪቱ በሕገወጥ የገቡ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር የማዋል እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል።
በትራምፕ ከቪዛ ቀነ ገደባቸው በላይ የሚቆዩ ናቸው በተባሉ በርካታ አገራት ላይም የጉዞ እገዳ መጣላቸው አይዘነጋም። ከእነዚህ አገራት መካከል ኤርትራ፣ ቻድ፣ ሄይቲ፣ ምያንማር እና የመን ይገኙበታል።
ከእዚህ በተጨማሪም የትራምፕ አስተዳደር ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችላቸውን የቪዛ የቆይታ ጊዜ ያሳጠረ ሲሆን ለአንድ ጊዜ የሚያገለግል አድርጎታል።
ጥር ወር ላይም አስተዳደራቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጨምሮ ከ75 አገራት ለሚሄዱ ሰዎች የስደተኝነት ቪዛ የሚሰጥበትን ሂደት ላልተወሰነ ጊዜ ማገዱን አስታውቆ ነበር።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ከሚወዳደሩበት ጊዜ አንስቶ የስደተኞች ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው የነበረ ሲሆን፣ ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ አንስቶ በርካታ ስደተኞችን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተግባራዊ እደያረጉ ነው።















