ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማልኮም ኤክስ ግድያ በስህተት ለ20 ዓመታት የታሰረው ግለሰብ 40 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጠየቀ
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹን ማልኮም ኤክስን ገድለሃል ተብሎ በስህተት ጥፋተኛ ተብሎ 20 ዓመታትን በእስር ያሳለፈው ሙሃመድ አዚዝ ኒው ዮርክ ከተማ 40 ሚሊዮን ዶላር እንዲክሰው ጠየቀ።
ሙሃመድ አዚዝ የማልኮም ኤክስን ግድያ ተከትሎ ከታሰረ ከ20 ዓመታት በኋላ ከእስር የተለቀቀው በ1985 ነበር።
በ2021 ዐቃቤ ሕግ አዲስ ማስረጃ አግኝቻለሁ በሚል ሙሃመድ አዚዝ ወንጀሉን አልፈጸመም ብሏል።
የቀድሞ የባሕር ኃይል አባሉ ሙሃመድ አዚዝ በ1965 ሲታሰሩ የ6 ልጆች አባት እና የ26 ዓመት ወጣት ነበሩ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማልኮም ኤክስ የአደባባይ ንግግር ለማድረግ ዝግጅት ላይ እያለ በታጠቁ ሦስት ሰዎች በጥይት ተደብድቦ ነበር የተገደለው።
በወቅቱ በግድያው ተጠርጥሮ ሙሃመድ አዚዝ ከካህሊል ኢስላም ጋር ነበር የታሰረው። 22 ዓመታትን በእስራት ያሳለፈው ኢስላም በ2009 ሕይወቱ አልፏል።
ዐቃቤ ሕግ ተጨባጭ ማስረጃ ሳያቀርብ፤ የሚጣረስ ሃሳብ የሰጡ ምስክሮችን አሰምቶ በሁለቱ ግለሰቦች ላይ ብይን ያሰጠው።
ግድያው በተፈጸመበት ቦታ በቁጥጥር ሥር የዋለው እና ማልኮም ኤክስን መግደሉን ያመነው ታለማደግ ሃዬር፤ በሁለቱ ግለሰቦች የፍርድ ሂደት ላይ ቀርቦ በወንጀሉ እጃቸው የለበትም ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር።
በ1970ዎቹ ደግሞ በግድያው ሌሎች አራት ሰዎች መሳተፋቸውን ሃየር የጽሑፍ ቃለ መሃላ ፈጽሟል።
በ2020 የእነ ሙሃመድ ጉዳይ ተጣርቶ ንጽህናቸው እንዲረጋገጥ ክሱን እንደገና ማየት ተጀምሮ ነበር። የሁለቱን ተጠርጣሪዎች ጥብቅና የያዘው ዴቪድ ሻኒስ፣ በመንግሥት ግዴለሽ አሰራር ምክንያት ሁለቱ ሰዎች በስሕተት 42 ዓመታትን እስር ቤት እንዲያሳልፉ ተደርገዋል ብሏል።
“የዘገየ ፍርድ እንደተነፈገ ይቆጠራል። ሙሃመድ አዚዝ 84 ዓመታቸው ነው። ኢስላም ደግሞ እንዳለመታደል ሆኖ ንጽህናቸው ሳይረጋገጥ ሕይወታቸው አልፏል” ብሏል ጠበቃው ዴቪድ።
ባለፈው ዓመት የማልኮም ኤክስ ልጅ የአባቴ ጉዳይ እንደገና ይታይልኝ በማለት አመልክታ ነበር።
የማልከም ኤክስ ሴት ልጅ በግድያው ወቅት ፖሊስ የነበረ ሰው ጽፎ አስቀምጦታል ያለችውን ደብዳቤ በመጥቀስ ግድያውን ያቀነባበሩት ኤፍቢአይ እና የኒው ዮርክ ፖሊስ ናቸው ብላለች።
እነዚህ ማስረጃዎች ተደማምረው 20 ዓመታትን በእስር ያሳላፉት የ84 ዓመቱ ሙሃመድ አዚዝን በኒው ዮርክ ከተማ ላይ ክስ እንዲመሰርቱ አድርጓቸዋል።
ያላአግባብ እና በመንግሥት ግዴለሽ አሰራር ምክንያት ለታሰሩበት ለሁለት አስርት ዓመታትም 40 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።