ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ ባለቤት ሕይወታቸው አለፈ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ ባለቤት ኢቫና ትራምፕ በ73 ዓመታቸው ሕይወታቸው አለፈ።
ሞታቸውን ተከትሎ የቀድሞው ባለቤታቸው ዶናልድ ትራምፕ በራሳቸው የማሕበራዊ ትስስር ገጽ የተሰማቸውን ሐዘናውን ገልጸዋል።
“ትልቅና ተምሳሌታዊ ሕይወት መምራት የቻለች፣ ጎበዝ፣ ቆንጆ እና አስደናቂ ሴት ነበረች” ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ።
ኢቫና ትራምፕ የተወለዱት በአሁኗ ቼክ ሪፐብሊክ ነበር። ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በፈረንጆቹ 1977 ትዳር መስርተው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል። ከ15 ዓመታት የትዳር ሕይወት በኋላ ግን በ1992 ተለያይተዋል።
እንደ አሶሼትድ ፕረስ ዘገባ ከሆነ ሞታቸው አደጋ ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ግምቱን አስቀምጧል።
ምንጮች እንደሚሉት ኢቫና ትራምፕ ኒው ዮርክ ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው የመወጣጫ ደረጃ ላይ ወድቀው ራሳቸውን ስተው ነው የተገኙት። የሞታቸው መንስኤ ምናልባትም ከደረጃ መውደቅ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ዶናልድ እና ኢቫና በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ ዝነኞች የነበሩ ሲሆን ፍቻቸውም በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከተፋቱ በኋላ ኢቫና የራሳቸውን የመዋቢያ፣ ልብስ እና ጌጣጌጥ ንግድ ከፍተው ሲሰሩ ቆይተዋል።
ኢቫና ከትራምፕ የወለዷቸውን ዶናልድ ጆኒየር፣ ኢቫንካ እና ኤሪክ በሙሉ ኃላፊነት ማሳደጋቸውን ይነገራሉ።
ኢቫና በመጽሃፋቸው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ከተለያዩ በኋላ ወዳጅነታቸው ከፍ ያለ ሲሆን ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ያወሩ እንደነበር አብራርተዋል።
የመጀመሪያ ልጃቸው ኢቫንካ በእናቷ ሞት እጅጉን ማዘኗን እና እናቷ በጣም ጠንካራ፣ ለዓላማዋ የምትኖር እና አርዓያ እንደነበረች ገልጻለች።
ዶናልድ ትራምፕ ለኢቫና ሁለተኛ ባል ናቸው። የመጀመሪያ ባለቤታቸው ኦስትሪያዊው አልፍሬድ ዊንክልሜር የተባሉ ግለሰብ ናቸው። ጋብቻውን የፈጸሙት የኦስትሪያ ዜግነት ለማግኘት እንዲያስችላቸው ነው ይባላል።
የኦስትሪያ ዜግነትም በወቅቱ በኮሚኒስት ስርዓት ትተዳደር የነበረችውን ችኮዝላቫኪያ ለቀው እንዲወጡ አስችሏቸዋል።
በ1970ዎቹ ካናዳ ውስጥ ሲኖሩ በበረዶ ሸርተቴ አስተማሪነት እና በሞዴልነት ሲሰሩ ቆይተዋል።
እአአ 1976 ወደ ኒው ዮርክ ያደረጉት ጉዞ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር እንዲገናኙ በር ከፈተላቸው። ከዚያም በሚቀጥለው ዓመት ተጋብተው የጋዜጦች የፊት ገጽ ማድመቂያ መሆን ጀመሩ።
በትዳር ዘመናቸው ኢቫና ብዙ የትራምፕ ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ኢቫና ትራምፕ በ2017 ለኤቢሲ እንደተናገሩት ወደ ዋይት ሓውስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር በመደወል ባለቤታቸው ማላኒያን ለማስቀናት እንደማይሞክሩ ተናግረው ነበር። “በመሰረቱ እኔ የትራምፕ የመጀመሪያ ሚስት ነኝ። እሽ? ስለዚህ እኔ ነኝ ቀዳማዊት እመቤት” በማለት የቀለዱት ከማይረሱ ንግግራቸው መካከል አንዱ ነው።
በ1990 ግን የሁለቱ ጥንዶች ትዳር መፈረካከስ ጀመረ።
አለመስማማቱ እያየለ ሲመጣ በ1992 ጥንዶቹ ሲለያዩ ኢቫና 14 ሚሊዮን ዶላር እና ሌሎች ንብረቶችን ተካፍለዋል።
ከዚያም በኋላ ኢቫና ሁለት ጊዜ ትዳርን ሞክረውታል። ሁለቱም የትዳር አጋሮቻቸው ጣሊያናውያን ነበሩ። የመጀመሪያው ሪካርዶ ማዙቺሊ የተባሉ ነጋዴ ሲሆኑ ትዳራቸው ከ1995 እስከ 1997 ቆይቷል። ሁለተኛው ደግሞ ሮሳኖ ሩቢኮንዲ የተባለ የትወና ባለሙያ ሲሆን ከ2008 እስከ 2009 ለ1 ዓመት ቆይተዋል።