ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ የኃላፊው ያለመከሰስ መብት ተነሳ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል እና የአዲስ አበባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ሙሉቀን ሀፍቱ (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት ተነሳ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የአባሉን የሙሉቀን ሀፍቱ (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የወሰነው ከፍትሕ ሚንስቴር የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ ነው።
ፍትሕ ሚንስቴር የአዲስ አበባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሙሉቀን ሀፍቱ (ዶ/ር) የሕግ ከለላ እንዲነሳ የጠየቀው በቅርቡ ከወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ አወጣጥ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንዲደረግባቸው ለማድረግ ነው።
ከሁለት ቀናት በፊት ሙሉቀን ሃብቱ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጎ እንደነበረ ይታወሳል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የሁሉም የክልል እና ከተማ ምክር ቤት አባላት እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር ያለመከስሰሰ እና በቁጥጥር ሥር ያለመዋል ሕጋዊ ከለላ አላቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ቻርተር አዋጅ አንቀጽ 4 ማንኛውም የከተማ መስተዳድሩ ምክር ቤት አባል ወንጀል ሲፈዕም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም ሲል ይደነግጋል።
የምክር ቤት አባላት በወንጀል ሲጠረጠሩ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የሚያደርገው የተወከሉበት ምክር ቤት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልቃድር የፍትህ ሚኒስትር ለምክር ቤቱ የላከውን ደብዳቤ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ሙሉቀን ሀፍቱ ስልጣንናቸውን እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመጠቀም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንዲደረግባቸው ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ጠይቋል ሲሉ አፈጉባኤዋ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
ይህንንም ጥያቄ ተከትሎ የከተማው ምክር ቤት በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ባለው ጉባኤ የምክር ቤቱ አባል ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ወስኗል፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ማውጣት ሂደት ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተያያዘ አስር ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው መገለጹ ይታወሳል።
የከተማ አስተዳደሩ የእጣ ማውጫ ሶፍትዌር ውስጥ የገባው መረጃ የተቀነባበረ ነው ብሏል። ይህንንም ተከትሎ የዕጣ ማውጣት ሂደቱ ተዓማኒነት የለውም በማለት ዕጣው ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲሆን መደረጉን ይታወሳል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የቴክኖሎጂ ውንብድና አጋጥሞናል፣ ድርጊቱን አመራር የመራው ውንብድና ነው። በዚህ ሂደት የቤት ስርቆት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት ጭምር መግለጽ ይቻላል” ሲሉ ድርጊቱ ፖለቲካዊ አላማንም የያዘ ነው ብለዋል።
ከቀናት በፊት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የከተማው የኢኖቬሽን እና ኢንፎርሜሽን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አብርሀም ሰርሞሎ፣ ዳይሬክተሩ መብራቱ ወልደኪዳን ዳይሬክተር፣ .የቤቶች ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ኩምሳ ቶላና የሶፍትዌር ባለሙያዎች የሆኑት ፣ ሀብታሙ ከበደ፣ ዮሴፍ ሙላት፣ ጌታቸው በሪሁን፣ቃሲም ከድር፣ ስጦታው ግዛቸው፣ ባየልኝ ረታ፣ ሚኪያስ ቶሌራ መሆናቸውን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።