ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ካንዬ ዌስት ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደር ይፋ አደረገ
በበርካታ ውዝግቦች ውስጥ የቆየው የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ካኒዬ ዌስት ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደሚወዳደር አስታወቀ።
በቅርቡ ‘ዬ’ ተብሎ እንዲጠራ ስሙን የቀየረው ታዋቂው ሙዚቀኛ፣ በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ላይ መለያው ሆኖ የሚያገለግለውን አርማውን የሚያሳይ ቪዲዮ “ዬ 24” ከሚል ጽሁፍ ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ አድርጓል።
ጨምሮም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋራ አብረውት እንዲወዳደሩ እንደጠየቃቸው ገልጿል።
ዌስት በቀደመው ምርጫ ላይ ለፕሬዝዳንትንት ተወዳድሮ የነበረ ሲሆን፣ የምርጫ ዘመቻው 70,000 ድምጽ ብቻ ነበር ያስገኘለት።
ለቀጣዩ ምርጫ እንደሚወዳደር ይፋ ያደረገው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ ስፍራ ከታዋቂው የነጭ ብሔረተኛ ኒክ ፉነቴስ ጋር ከታየ በኋላ ነው።
ካንዬ ዌስት ትራምፕ አብረውት እንዲወዳደሩ እንደጠየቃቸውና በቁጣ ለፕሬዝዳንትነት ውድድር መቅረቡን እንደተቃወሙት እንዲሁም የተለያየ ጥያቄ እንዳቀረቡለት ገልጿል።
ዌስት በአውሮፓውያኑ 2024 በሚካሄደው የአሜሪካ ለፕሬዝዳንትነት ዕጪ ሆኖ ለመመረጥ የሚያስችውን ዘመቻ የጀመረው ስሙን የሚያጠፉ በርካታ ውዝግቦች መቀስቀሳቸውን ተከትሎ ነው።
የ45 ዓመቱ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዌስት፣ ከነጮች እና ከአይሁዳውያን ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን ከሰጠ በኋላ ውዝግብ የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የሰጣቸው ቃለ ምልልሶችም የበለጠ ውዝግቡን አባብሶት ቆይቷል።
በዚህም ሳቢያ ከዌስት ጋር አብረው ሲሰሩ የነበሩት ጋፕ እና አዲዳስን የመሳሰሉ ታዋቂ የፋሽን ኩባንያዎች ስምምነታቸው አቋርጠዋል።
ይህንንም ተከትሎ ዌስት ከደንበኞቹ ጋር የነበረው የሥራ ውል በመቋረጡ ምክንያት “ሁለት ቢሊዮን ዶላር በአንድ ቀን ማጣቱን” አሳውቋል።
ዌስት ለቀጣዩ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድድሩ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻው ኃላፊ የሰየመ ሲሆን፣ ግለሰቡም በጽንፈኛ አመለካከቱ የሚታወቅና በተለያዩ ጉዳዮች ውዝግብ ውስጥ የቆየ መሆኑ ይነገራል።