ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤሎን መስክ ከዚህ ቀደም በትዊተር የታገዱ አካውንቶችን ሊመልስ ነው
ኤሎን መስክ ከዚህ ቀደም በትዊተር የታገዱ አካውንቶችን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሊመልስ ነው።
የትዊተር አዲሱ ባለቤት ኤሎን መስክ እንዳለው “ ምህረት” አደርጋለሁ ብሏል።
ኤሎን መስክ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ለትዊተር ተጠቃሚዎች “ህግን ያልጣሱ ወይም በአስደንጋጭ ሁኔታ ያጭበረበሩ” አካውንቶችን ባላካተተ መልኩ ሌሎች የታገዱ አካውንቶች እንዲመለሱ የሚጠይቅ የህዝብ አስተያየትንም ሰብስቧል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ አካውንቶች እገዳቸው የተነሳላቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይገኙበታል።
የዓለማችን ባለጸጋው መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር የገዛው ባለፈው ወር ነበር።
ከ3.1 ሚሊዮን በላይ የትዊተር ተጠቃሚዎች ለመስክ ድምጽ ስጡ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 72.4 በመቶ የሚሆኑት እገዳው እንዲነሳ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ህዝቡ ፈርዷል። ምህረት ማድረግ በሚቀጥለው ሳምንት ይጀምራል” በማለት በትዊተር 118.7 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ኤሎን መስክ በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
መስክ በተጨማሪም “የህዝብ ድምጽ የአምላክ ድምጽ ነው” የሚለውን የላቲን ሐረግም ተጠቅሟል።
ኤሎን መስክ የይቅርታው ሂደት እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆን ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የትዊተር ተጠቃሚዎች ይሁንታን አግኝቻለሁ በማለት የዶናልድ ትራምፕን እገዳ አንስቷል።
ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ወደ ማህበራዊ ሚዲያው ለመመለስ “ምንም ምክንያት አይታየኝም” ማለታቸው ወደ ትዊተር ላይመለሱ ይችላል የሚለው ጠቋሚ ነው ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የትዊተር ገጻቸው የታገደው ባለፈው ዓመት ሲሆን ይህም ግጭትን እና ሁከትን በማነሳሳት በሚል ነበር።
የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ካፒቶል ሂል ጥሰው ከገቡ ከቀናት በኋላ የትዊተር የቀድሞ አስተዳደር እርምጃ ወስዷል።
መስክ ከትራምፕ በተጨማሪ የራፐር ዬ (የቀድሞው ካንዬ ዌስትና የተፅእኖ ፈጣሪውን አንድሪው ታቴ የትዊተር አካውንታቸው እንዲመለስ አድርጓል።
ሆኖም ባለጸጋው ኤሎን የሴራ ጽንሰ ሃሳብ ተንታኙ አሌክስ ጆንስ ወደ ትዊተር እንዲመለስ አይፈቀድለትም ብሏል።
የኢንፎዋርስ የተሰኘው ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ጆንስ በአውሮፓውያኑ 2012 ሳንዲሁክ ትምህርት ቤት 20 ህጻናትንና ስድስት ጎልማሶችን የቀጠፈው ጥቃት ውሸት ነው በማለቱም 1.44 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተገድዷል።
መስክ እንዳለው "የልጆችን ሞት ለጥቅም፣ ለፖለቲካ ወይም ለዝና ለሚጠቀም" ለማንኛውም ሰው "ምንም አይነት ምህረት እንደሌለው" ጽፏል።