ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕን የታክስ ጉዳይ በዲሞክራቶች በተያዘው ኮሚቴ እንዲታይ ፈቀደ
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን የታክስ ሰነዶች በዲሞክራቶች ቁጥጥር ስር ያለ የምክር ቤት ኮሚቴ እንደመለከተው መንገዱን አመቻቸ።
ባለፈው ትራምፕ ከስር ያሉ ፍርድ ቤቶች የፋይናንስ ሰንዶቻቸውን እንዳይመለከቱ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ጥያቄቸውን ውድቅ አድርጓል።
ውሳኔው ለዓመታት ከታክስ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ምስጢር አድርገው ለቆዩት ትራምፕ ያልተጠበቀ ነው።
ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ከታክስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይፋ ባለማድረግ በ40 ዓመታት ውስጥ ትራምፕ የመጀመሪያው ናቸው።
በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የሚገኝ ኮሚቴ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ የትራምፕን የታክስ ሰነድ ለመመልከት ሲጠይቅ ነበር።
ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን ዘመቻ የጀመሩት ትራምፕ ከተሰማሩበት የቢዝነስ ሥራ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ምርመራዎች ተካሂዶባቸዋል።
ትናንት ማክሰኞ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው በዚህ ውሳኔ ላይ ጉዳዩን ከተመለከቱት ዳኞች የተቃወመው የለም።
ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንደ አውሮፓውያኑ ከ2015 እስከ 2020 ያለውን የትራምፕ እና ከተወሰነ የንግድ ሥራዎቻቸው ጋር የተገናኙ የታክስ ሰነዶችን በምክር ቤቱ ስር ለተዋቀረው ኮሚቴ አሳልፎ ይሰጣል።
የትራምፕን ሰነዶች የሚመለከተው ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት የምክር ቤት አባሉ ሪቻርድ ኔል ባወጡት መግለጫ ላይ “ከሦስት ዓመት በላይ ስንጠይቅ የነበረውን ቁጥጥር የማድረግ ሥራን አሁን እንጀምራልን” ብለዋል። ነገር ግን ኮሚቴው የትራምፕን የታክስ ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ ማድረግን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።
በትራምፕ የተሾሙት የይግባኝ ፍርድ ቤት ዳኛ ዋሽንግትን ውስጥ ባለፈው ዓመት ባሳለፉት ውሳኔ፣ ምክር ቤቱ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሰነዶች የመመርመር ሕጋዊ መሠረት አለው በማለት ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
ኮሚቴው የትራምፕን መዛግብት በመመርመር የታክስ ባለሥልጣናት የፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎችን የታክስ ሰነዶች በአግባቡ ኦዲት ማድረጋቸውን እና አዲስ ሕግ አስፈላጊ እንደሆነ ለመወሰን እንዳሰቡ ገልጸዋል።
ኮሚቴው በሥራ አስፈጻሚው እና በሕግ አውጪው ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር እንዳያካሂድ ትራምፕ እምቢተኛ ሆነዋል በማለት ጉዳዩን ወደ ታችኛው ፍርድ ቤት ወስዶት ነበር።