የሊባኖስ ባንኮች ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት አቆሙ

ታትሟል

የሊባኖስ ባንኮች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አስፈላጊውን ጥበቃ አላደረጉልንም በሚል ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ የአገሪቱ ባንኮች ማኅበር ገለጸ።

ደንበኞች ባለፈው ሳምንት እንዳይንቀሳቀስ የተደረገውን የቁጠባ ሂሳባቸውን ለማግኘት በኃይል ታግዘው ገንዘባቸውን የመውሰድ ድርጊቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ነው የሊባኖስ ባንኮች ማኅበር አገልግሎት መቆሙን ያስታወቀው።

በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች መፍትሄ ማግኘት ያልቻሉ የደኅንነት ስጋት ገጥሟቸዋል ሲልም ማኅበሩ ገልጿል።

ባሳለፍነው ሳምንት አንዲት ግለሰብ የልጆች መጫወቻ ሽጉጥ በመያዝ ለቤተሰቧ መድኃኒት መግዣ የሚሆን ገንዘብ ከባንኩ ለመውሰድ በባኩ ውስጥ ሰዎችን በማገቷ መነጋገሪያ ሆና ነበር።

በሳምንቱ መጨረሻ አርብ ቀን ብቻ ቢያንስ አምስት ሰዎች ገንዘባቸውን በኃይል ከባንክ ለመውሰድ ጥረት ያደረጉበት ተመሳሳይ ክስተቶች ሪፖርት ተደርገው ነበር።

በአሁኑ ጊዜ ሊባኖስ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ የምግብ እና የመድኃኒት አቅርቦት ለማግኘት የሚያስችለው ገቢ የለውም።

ደንበኞች በባንኮች ውስጥ ያላቸውን ገንዘብ በኃይል በመጠቀም የመውሰድ እምጃ በሕበረተሰቡ ዘንድ ድጋፍ አግኝቷል።

ከዚህ በፊት ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌላቸው ሰዎች የባንክ ሂሳባቸውን በጉልበት ለማንቀሳቀስ መጣራቸው በሕብረተሰቡ ዘንድ በተስፋ መቁረጥ ተገፋፍቶ የሚፈጸም ተደርጎ ይታያል።

የሊባኖስ የመገበያያ ገንዘብ እኤአ ከ2019 ጀምሮ ዋጋው እያሽቆቆለ፣ ብሎም በአገሪቱ ያለው የዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን ተከትሎ ባንኮች ደንበኞቻቸው የሚያወጡትን ገንዘብ ገድበዋል።