ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊባኖስ፡ ኢማኑዔል ማክሮ በቤይሩት አዲስ መንግሥት እንዲዋቀር ጥሪ አቅርበዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ በሊባኖስ አዲስ መንግሥት በፍጥነት እንዲመሠረት ጥሪ አቀረቡ።
ማክሮ ይህን ያሉት ሊባኖስ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ማግኘቷን ተከትሎ ነው።
በጀርመን የሊባኖስ አምባሳደር የነበሩት ሙስጠፋ አዲብ የበርካታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ድምጽን በማግኘት ነው ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት።
ከፍተኛ የሊባኖስ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ሙስጠፋ አዲብ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው እንዲሾሙ የማክሮ ተጽእኖ አለበት።
ከዚህ ቀደም በስልጣን ላይ የነበረው የሊባኖስ መንግሥት የቤይሩቱን ፍንዳታ ተከትሎ ከሥልጣን መውረዱ ይታወሳል።
ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ በመዲናዋ ተከማችቶ የነበረው አልሙኒየም ናይትሬት ፈንድቶ ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም።
ይህ ፍንዳታ ካጋጠመ ለሁለተኛ ጊዜ ማክሮን ሰኞ ዕለት ሊባኖስ ገብተዋል። ማክሮ በሊባኖስ በሚኖራቸው ቆይታ ባለስልጣናት ሙስናን እንዲዋጉ ጫና ያሳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ማክሮ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ በሊባኖስ አዲስ መንግሥት “በተቻለ ፍጥነት መመሠረት አለበት” ብለዋል።
አዲሱ ተሿሚ ጠቅላይ ሚንስትርም ይህንኑ ለመፈጸም ከዚህ ቀደም ቃል ገብተዋል።
ማክሮን ሊባኖስ በደረሱ ወቅት ተቃውሞም አጋጥሟቸው ነበር። ተቃዋሚዎች “አዲብ ጠቅላይ ሚንስትር መሆን የለባቸውም” የሚል እና ሌሎች መፈክሮችን በቤይሩት ጎዳናዎች ላይ አሰምተዋል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ሹመት ለፈረንሳይ ጣልቃ ገብነት የተመቻቸ እንዲሆን ተደርጎ የተከናወነ ነው የሚሉ ተቺዎች አሉ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ሹመት የመጣው የቤይሩት ፍንዳታ በበርካቶች ላይ ጉዳትን አስክትሎ እና የመዲናዋን መሠረተ ልማት ካፈራረሰ በኋላ እንዲሁም የሕዝብ ቁጣ ባየለበት ወቅት ነው። ከቤይሩቱ ፍንዳታ በፊትም የሊባኖስ መገበያየ ገንዘብ የውጪ ምንዛሬ አቅም እጅጉን ተዳክሟል። ሙስና እና ሥራ አጥነትም ተስፋፍቷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሙስጠፋ አዲብ ማናቸው?
የ48 ዓመቱ ሙስጠፋ በፈረንጆቹ 2013 ላይ በጀርመን የሊባኖስ አምባሳደር ሆነው ተሹመው ነበር። በሕግ እና የፖለቲካ ሳይንስ የዶክትሬት ምሩቅ የሆኑት ሙስታፋ፤ በሊባኖስ እና ፈረንሳይ በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረዋል። ለቀድሞ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አዲብ ከሹመታቸው በኋላ በአስቸኳይ አዲስ መንግሥት መመሠረት እንደሚያስፈልግ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ (አይኤምኤፍ) ጋር በመወያየት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።