ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቁጢጥ ብሎ መቀመጥ እንዴት ለጤና ጠቃሚ ሊሆን ቻለ?
ቁጢጥ የማለት ስፖርት (deep squat) ቻይና እና ጃፓንን ጨምሮ በአብዛኞቹ የእስያ አገራት የተለመደ ነው።
ባቡር ሲጠብቁ፣ ከጓደኛ ጋር ሲጨዋወቱ ወይም ምግብ ሲመገቡም ቁጢጥ ማለትን የሚያዘወትሩ ብዙ ናቸው።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ቱሪስቶች ቁጢጥ ለማለት ሲሞክሩ ያሳያሉ። አብዛኞቹ ቱሪስቶች በሙከራቸው ወቅት በጀርባቸው ተከንብለው ወይም ወደ ጎን ይወድቃሉ።
አንዳንዶች ሲንገዳገዱ ግድግዳ ይደገፋሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት ቁጢጥ ማለት ዝናው የናኘው ዕድሜ ሲገፋ ሰውነት በጥሩ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ የሚደረዳ በመሆኑ ነው።
አንዳንዶች በቀላሉ ቁጢጥ ሲሉ ሌሎች ግን ሰውነታቸው አልታዘዝ የሚላቸው ለምን ይሆን?
ቁጢጥ ማለት ለጤና ይጠቅማል?
ቁጢጥ ማለት ሰውነት ከሚያደርጋቸው ቁልፍ እንቅስቃሴዎች አንደኛ ነው።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳውዝ ካሊፎርንያ የሰውነት እንቅስቃሴ ባለሙያ ፕሮፌሰር ክሪስቶፈር ፓወርስ "ቁጢጥ ሳይባል ምንም ነገር ማከናወን አይቻልም" ይላሉ።
"ወንበር ላይ እንቀመጣለን፤ ከወንበር እንነሳለን፤ መፀዳጃ ቤት እንቀመጣለን፤ እቃ ከመሬት ለማንሳት እናጎነብሳለን።"
ቁጢጥ ማለት የተመለደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዓይነት ነው። ነገር ግን በእስያ የሚዘወተረው ቁጢጥ ማለት (Asian squat) ከዚህ ይለያል።
ዲፕ ስኳት (deep squat) ወይም ፉል ስኳት (full squat) በሚል ስያሜ የሚታወቀው ቁጢጥ የማለት መንገድ ጉልበትን እስከመጨረሻው ድረስ አጥፎ፣ እግርን ከፍቶ፣ ደረትን ነፍቶ፣ ጀርባ ጭን ላይ አርፎ የሚከናወን ነው።
እስያዊ አሜሪካዊው ማት ህሱ ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን እንዲያጠነክሩ እና አካላቸውን እንዲያዳብሩ ሥልጠና ይሰጣል።
በእስያውያን ዘንድ ስለሚዘወተረው ቁጢጥ የማለት ስፖርት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቃቸው ቪድዮዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች አግኝተዋል።
ባለሙያው እንደሚለው "በእስያውያን የሚዘወተር ቁጢጥ ማለት" የሚለው ስያሜ ትክክለኛ መልዕክት አያስተላልፍም።
"አፍሪካውያን የእኛ ነው ይላሉ። የምሥራቅ አውሮፓ አገራትም የእኛ ነው ይላሉ። ቁጢጥ ማለት የሁሉም ነው።"
ይህ ቁጢጥ ማለት የወገብ፣ የጉልበት እና ቁርጭምጭሚት እንቅስቃሴ ይጠይቃል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከተለመደው ቁጢጥ ማለት በበለጠ የሰውነት ክፍሎች ላይ ስሜቱ ጎልቶ ይስተዋላል።
ቁጢጥ ሲባል ሰውነት ላይ የሚፈጠረው ከፍተኛ መሳሳብ ወይም መወጣጠር የሰውነት መታዘዝን የሚያቀላጥፍ እና የጀርባ ሕመምን የሚቀንስ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።
ሰውነት ድጋፍ ሳያሻው ሕይወትን ለመግፋትም መንገድ ይከፍታሉ።
ልጆች ብዙም መጣጣር ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ ቁጢጥ ማለት ይችላሉ።
ለዚህም ምክንያቱ የሰውነት መገጣጠሚያቸው በቀላሉ መንቀሳቀስ ስለሚችል ነው። የሰውነታቸው ክብደትም ከአዋቂዎች የተለየ መሆኑ ያግዛቸዋል።
አዋቂዎች ቁጢጥ ለማለት የሚቸገሩት ሰውነታቸው ስለሚለወጥ ብቻ አይደለም።
የአኗኗር ዘዬ ቁጢጥ የማለት ችሎታን ለውጧል። ወንበር መጠቀም ማዘውተር እና የመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ከፍ ማለት ተጠቃሽ ናቸው።
በአኗኗር ለውጥ ምክንያት አዋቂዎች ቁጢጥ የሚሉበት ዕድል እያገኙ አይደለም። ስለዚህም በጊዜ ሒደት የሰውነት ቅልጥፍናቸው ላይ ጫና ያሳድራል።
የሰውነት እንቅስቃሴ ባለሙያ ፕሮፌሰር ክሪስቶፈር ፓወርስ "ሰውነት ጥቅም ላይ ካልዋል ጥቅም መስጠቱን ያቆማል" ይላሉ።
እስያውያን ለምን በቀላሉ ቁጢጥ ይላሉ?
የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ጃፓንን ጨምሮ በሌሎችም የእስያ አገራት ይስተዋላል።
ለምሳሌ ሬስቶራንት ውስጥ ለመመገብ ቁጢጥ ማለት ያስፈልጋል።
ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን እንዲያጠነክሩ እና አካላቸውን እንዲያዳብሩ ሥልጠና የሚሰጠው እስያዊ አሜሪካዊው ማት ህሱ "ሬስቶራንት ገብቶ ጫማ አውልቆ ምንጣፍ ላይ ቁጢጥ ብሎ መቀመጥ የተለመደ ነው" ይላል።
መሠረታዊ የሆኑ ሌሎች የሰውነት እንቅስቃሴዎችም የጭን እና እግር ጥንካሬን ይጠይቃሉ።
"በአንዳንድ የእስያ ክፍሎች መፀዳጃ ቤቶች መጠቀም የሚቻለው ቁጢጥ ብሎ ብቻ ነው። ይህም ቁጢጥ የማለት ችሎታን ያዳብራል" ሲል ባለሙያው ያስረዳል።
ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርግ የተወሰነ እረፍት ብቻ እየወሰደ ለ40 ደቂቃ ቁጢጥ ብሎ ነበር።
በቤተሰብ ተሞክሮው ምክንያት ቁጢጥ ማለት ያለውን ጠቀሜታ ተረድቷል።
"አባቴ መንገድ ላይ ወድቆ መነሳት ስላልቻለ አምቡላንስ መጥራት የግድ ሆኖ ነበር" ሲል ያስታውሳል።
በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ሳለ ቁጢጥ የማለት ችሎታው ለተወሰነ ጊዜ ተዳክሞ ነበር።
"ሰውነቴ ከመወጠሩ የተነሳ ጉልበቴን መንካት እንኳን አልችልም ነበር" ይላል። ሰውነቱ በድጋሚ ቁጢጥ ማለትን እንዲላመድ ማሠልጠን ነበረበት።
እንደማንኛውም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቁጢጥ ማለትንም መማር እንደሚቻል ያስረዳል።
በእስያውያን የሚዘወተረውን ቁጢጥ የማለት ስፖርት ለመልመድ በአንድ ጊዜ ሰውነትን ማስገደድ እንደማይገባ ይመክራል። ሰውነት ቀስ በቀስ እንቅስቃሴውን እንዲላመድ ማድረግ ይመረጣል።
"ሰውነትን ማስገደድ እና ማጣደፍ ለጉዳት ይዳርጋል" ሲል ባለሙያው ያስጠነቅቃል።
ቀስ በቀስ ሰውነትን ማላመድ እና ቁሳቁስ በመደገፍ ሰውነትን ማባበልን ይመክራል።
ሰውነት ቁጢጥ ማለት እንስከሚችልበት ርቀት ድረስ ማንቀሳቀስ እና በዝግታ ማላመድ እንደሚያሻ ይናገራል።
"በቀን ሁለት ጊዜ ይሄንን ካደረጋችሁ በጥቂት ሳምንታት ለውጥ ታያላችሁ። ቀስ በቀስ ሰውነታችሁ ወደታች የሚወርድበት ርቀት ይጨምራል።"
ዕድሜ ሲገፋ ቁጢጥ ማለትን ለሰውነት የማስተማር ነገር አጠያያቂ ይሆናል።
እስያዊ አሜሪካዊው ማት ህሱ "ዕድሜ ሲገፋ የመገጣጠሚያ የመንቀሳቀስ አቅም ይዳከማል፤ በተለይ ደግሞ የወገብ እና የጉልበት አቅም ሲዳከም ቁጢጥ ማለት ያስቸግራል" ሲል ያብራራል።
በየትኛውም መጠን ቁጢጥ ማለት ለሰውነት እንደሚጠቅም ጥናቶች ያሳያሉ። ነገር ግን የጉልበት፣ ወገብ እና ጀርባ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ይሄን እንዲያደርጉ አይመከርም።
በሕክምና ወቅት ቁጢጥ የማለት ልምምድ የሚደረገው እንደየታካሚው የሰውነት ዓይነት ወይም እንደደረሰው ጉዳት መጠን በመወሰን ነው።
"ሁሉም ሰው የራሱ መንገድ አለው። ሁሉም ሰው የተለያየ ነው" ይላል ባለሙያው።
የጭን አጥንታቸው አጭር የሆነ፣ የጉልበት እንቅስቃሴያቸው የደከመ ወይም የተለየ የወገብ አወቃቀር ያላቸው ሰዎች ሰውነታቸው የተስተካከለ ቢሆንም ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ሊቸገሩ ይችላሉ።
ዋናው ጥያቄ ምን ያህል ወገብን ዝቅ አድርጎ ቁጢጥ ማለት ይቻላል ሳይሆን፤ ዕድሜ ሲገፋ ምን ያህል እንቅስቃሴውን ማስቀጠል ይቻላል የሚለው ነው።
በየቀኑ ቁጢጥ ማለትን የረዥም ጊዜ ልማድ ያደረጉ ሰዎች በሒደት ለጤናቸው የሚሰጣቸው ጠቀሜታን በተመለከተ ጥናት አልተሠራም።
ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን እንዲያጠነክሩ እና አካላቸውን እንዲያዳብሩ የሚያሠለጥነው እስያዊ አሜሪካዊው ማት ህሱ ዘመናዊ አኗኗር ቁጢጥ ማለት ላይ ያሳደረውን ጫና መለወጥ ይፈልጋል።
"ከግል ተሞክሮዬ ተነስቼ ሰውነትን መቆጣጠር ያለውን ሚና እናገራለሁ" ይላል።