ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ከትራምፕ ጋር የገቡት አለመግባባት ተካርሮ ላቀረቡባቸው ትችት ዳግመኛ ምላሽ ሰጡ
የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ዶናልድ ትራምፕ ባላቸው ፖለቲካዊ ታዋቂነት ላይ ጥያቄ ካነሱ እና ዳግመኛ ፎቶ እንድንነሳ "በተደጋጋሚ" ጠይቃኛለች ማለታቸውን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ምላሽ ሰጡ።
ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሯ "በጣሊያን ካላት እውቅና አንጻር የሠራችው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም" ሲሉ ተችተዋል።
አክለውም አሜሪካ ቴህራን "የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳታገኝ ወይንም እንዳትሰራ" ለመከላከል ያደረጉትን ጥረት አልደገፉም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሯን ከስሰዋቸዋል።
ሜሎኒ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ ትራምፕ "ምንም ትንኮሳ ሳይደርስባቸው በቋሚነት የሚፈጽሙት ትችት እርባና ቢስ ነው" ብለዋል።
"ስለ እኔ ዝነኝነት የአንተ ጓደኛ መሆን አያግዘውም፤ ከአንተ ጋርም ባለኝ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ አይደለም" ብለዋል።
"የእኔ ዝነኛነት ያንተ ጭንቀት ሊሆን አይገባም። በራስህ ላይ እንድታተኩር ሃሳብ አቀርባለሁ" ሱሉ አክለዋል።
ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር አሜሪካ የአየር ኃይሉን ጦር ሠፈር በኢራን ላላት ዘመቻ እንዳትጠቀም በማድረግ "ግዙፍ የሎጀስቲክ እንቅፋት" ፈጥረዋል ሲሉ ከስሰዋቸዋል።
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን የአገሪቱ የጦር ሠፈሮችን መጠቀም "ሁሌም የምናከብረው የመንግሥታችን ስምምነት ነው። ያ ደግሞ እኔ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሆንኩ ድረስ የሚጣስ አይሆንም" ብለዋል።
አርብ ዕለት ሜሎኒ ትራምፕ በፈረንሳይ በተካሄደው የቡድን ሰባት አገራት ጉባዔ ላይ ከእኔ ጋር ፎቶ ለመነሳት "ለመነችኝ" ሲሉ በተናገሩት መገረማቸውን አስታውቀው ነበር።
ትራምፕ በየካቲት ወር ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ ወዲህ የሁለቱ መሪዎች አለመግባባት እያደገ መጥቷል።
የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ በሚቀጥለው ሳምነት ወደ አሜሪካ ሊያድርጉት የነበረውን ጉዞ ሰርዘዋል።
ትራምፕ እና ሜሎኒ በዚህ ሳምንት ፈረንሳይ ውስጥ በተካሄደው የቡድን 7 ጉባኤ ላይ በቅርበት ሲነጋገሩ የታዩ ሲሆን፣ የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ኋላ ላይ ለጋዜጠኞች ግንኙነታቸው ላይ ለውጥ እንደሌለ እና "ምንም ዓይነት መወቃቀስ እንዳልተፈጠረ" ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ትራምፕ ከአንድ የጣሊያን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ "ፎቶ እንድነሳ ስትለምነኝ አሳዝናኛለች" ብለዋል።
ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትሯ "ስላናገርኳት ምናልባት ደስ ብሏት ይሆናል" ማለታቸውን የገለጸው ቴሌቪዥን ጣቢያው፤ ፕሬዝዳንቱ እንዲህ ያሉበትን የራሳቸውን የእንግሊዝኛ ንግግር ሳያሰማ በጣልያንኛ የተተረጎመውን አቅርቧል።
ይህንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ትራምፕ ያሉትን ሙሉ በሙሉ ባለማመን መገረማቸውን በኢንስታግራም ላይ ለሰባት ሚሊዮን ተከታዮቻቸው ባስተላለፉት አጭር የቪዲዮ መልዕክት ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህ ክስተት ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመ አለመሆኑን በመግለጽም "የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለአጋሮቻቸው እንዲህ ዓይነት ባህሪ ለምን እንደሚያሳዩ አላውቅም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።
"ነገር ግን ግን ማስታወስ ያለባቸው አንድ ነገር አለ፤ እኔም ሆንኩ ጣልያን ፈጽሞ ለምነን አናውቅም።"
በ2022 የጣልያንን ጠቅላይ ሚኒስትርነትን የያዙት ሜሎኒ በጥር 2025 በትራምፕ ሲመተ በዓል ላይ የተገኙ ብቸኛዋ የአውሮፓ አገር መሪ ሲሆኑ፣ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት መሪዎች እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት መካከል ድልድይ እንደሚሆኑ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።
ሜሎኒ አሜሪካ ከኢራን ጋር ያደረገችውን ጦርነት በግልጽ የተቃወሙ ሲሆን፣ ትራምፕ ሚያዝያ ላይ ከጣልያኑ ዕለታዊ ጋዜጣ 'ኮሪየር ዴላ ሴራ' ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ "[ሜሎኒ] ደፋር ትመስለኝ ነበር፤ ነገር ግን ተሳስቻለሁ" ብለዋል።
ትራምፕ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛን "በወንጀል ላይ ደካማ እንዲሁም በውጭ ፖሊሲ ረገድ መጥፎ ናቸው" በማለት ሲወቅሷቸው፣ ሜሎኒ ተቃውመዋቸው ነበር።