ኢትዮጵያውያንን በሕገ ወጥ መንገድ አዘዋውረዋል የተባሉ አራት የኬንያ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ታትሟል

ኢትዮጵያውያንን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር የተጠረጠሩ አራት የኬንያ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

መርማሪዎች በሕገ ወጥ መንገድ የተዘዋወሩ 37 ኢትዮጵያውያንን ከኬንያ መዲና ናይሮቢ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ በአንድ ቤት ውስጥ አግኝተዋቸዋል ተብሏል።

አራቱ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር የዋሉትም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲፈፀም በመርዳት ተጠርጥረው ነው ።

ኢትዮጵያውያኑ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ እያቀኑ መሆናቸውን ለኬንያ ባለስልጣናት መናገራቸውን የግል ጋዜጣ የሆነው ዘ ስታር ዘግቧል።

የቤቱን ባለቤት እንዲሁም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳትፈዋል የተባሉ ሌሎች አባላትን ለመያዝም ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።

ኬንያ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ለሚሞክሩ ኢትዮጵያውያን ተመራጭ የመሸጋገሪያ መንገድ እንደሆነች የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ አይኦኤም አስታውቋል።

ስደተኞቹ በአብዛኛው ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የመጡ ወንዶች ሲሆኑ በሞያሌ ድንበር በኩል ወደ ኬንያ በመግባት ወደ ታንዛንያ እና በመጨረሻም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያቀኑ ኤጀንሲው ገልጿል።

ከጥቂት ወራት በፊት በኬንያ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ኢትዮጵያዊ 31 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ በናይሮቢ የሚገኝ ፍርድ ቤት መበየኑ ይታወሳል።

ይበቃል ጌታቸው የተባለው ግለሰብ ከሁለት ዓመታት በፊት በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በመኖሪያ ቤቱ እጃቸው በሰንሰለት የታሰሩ 12 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ተገኝተው ነበር።

ከጥቂት ወራት በፊት በኬንያ መዲና ናይሮቢ ኢስሊ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ፖሊስ 30 ሰነድ አልባ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ስለማዋሉ ሪፖርት ተደርጓል።

20 ወንዶች እና 10 ሴቶች መዳረሻቸው እስካሁን ወዳልተገለጸ ቦታ ሊዘዋወሩ ሲሉ እንደተያዙ የኬንያን ፖሊስ ዋቢ አድርጎ ስታንዳርድ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ በማቻኮስ ግዛት አቲ ሪቨር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሕገ-ወጥ መልኩ ኬንያ የገቡ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።