ወደ ዩክሬን የከዳው ሩሲያዊ ፓይለት ‘በጥይት ተገደለ’

ታትሟል

በስፔን የተገደለው አንድ ግለሰብ ሩሲያን ከድቶ ወደ ዩክሬን ኮብልሏል የተባለው ሩሲያዊ ፓይለት መሆኑ ተገለጸ።

ማስኪም ኩዝሚኖቭ ባለፈው ዓመት ነበር የጦር ሄሊኮፕተሩን እያበረረ ወደ ዩክሬን ግዛት ዘልቆ በመግባት እጁን የሰጠው።

የስፔን ፖሊስ ባለፈው ሳምንት በአሊካንቴ ግዛት አቅራቢያ ስለተገደለው ሰው ማንነት በይፋ አልገለጸም።

ሆኖም የዩክሬን ደኅንነት የተገደለው ግለሰብ ሩሲያዊው ፓይለት ኩዝሚኖቭ መሆኑን ሰኞ እለት አረጋግጧል።

የደኅንነት ቃለ አቀባይ ለዩክሬን ጋዜጣ ዩክሬይንስካ ፕራቭዳ እንደተናገሩት” [ፓይለቱ] መሞቱን አረጋግጠናል… በዩክሬን ከመቆየት ይልቅ በስፔን ለመኖር ወስኖ ሄደ” ብለዋል።

“እኛ የምናውቀው ነገር ቢኖር የቀድሞ የትዳር አጋሩን አብራው እንድትኖር ከጠራት በኋላ በጥይት ተመትቶ መገኘቱን ነው” ብለዋል።

የስፔን ባለስልጣናት በበኩላቸው ሟቹ በሐሰተኛ የማንነት ሽፋን ሳይኖር እንዳልቀረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኩዝሚኖቭ አስክሬን በስፔን ምስራቃዊ የባህር ጠረፍ በምትገኘው በቪላጆዮካ ከተማ በሚገኝ የመኖሪያ ስፍራ የተገኘ ሲሆን አብሮት የተገኘውም የማንነት ሰነድ ትክክለኛ ዜግነቱን ቢያረጋግጥም የሰፈረው ስም ሌላ እንደሆነ የስፔን የዜና ወኪል ኢፌ ዘግቧል።

ገዳዮቹ የተጠቀሙበት መኪና ወንጀሉ ከተፈጸመበት ስፍራ አጠገብ ተቃጥሎ መገኘቱንም የስፔን የስለላ ድርጅት ለዜና ወኪሉ ኢፌ መግለጹም ተዘግቧል።

ኩዝሚኖቭ አገሩን ሩሲያን ከድቶ ከመኮብለሉ በፊት ስለ ውሳኔው የዩክሬን የስለላ አገልግሎትን አነጋግሮ ነበር።

“ዘመቻ ሲኒቲሺያ” በሚል ስያሜ የተሰጠው የማስኮብለል ተግባርም ፓይለቱ ኤምአይ-8 የተሰኘችውን ሄሊኮፕተር ከድንበር አካባቢ እያበረረ በምስራቅ ዩክሬን በኩል ዘልቃ እንድትገባም ያለመ ነበር።

ይህም ባለፈው ዓመት ነሐሴ ተሳክቷል።

በሄሊኮፕተሯ ተሳፍረው የነበሩ እና የፓይለቱን እቅድ ያላወቁ ሌሎች ሁለት ሰዎች ሄሊኮፕተሯ ካረፈች በኋላ ወደ ድንበሩ መሮጥ ሲጀምሩ በጥይት ተገድለዋል። በወቅቱ እግሩ ላይ የተመታው ኩዝሚኖቭም ለግለሰቦቹ ግድያ ተጠያቂው የሩሲያ ጦር መሆኑን ተናግሮ ነበር።

ኩዝሚኖቭ ለዚህ ውሳኔ ያደረስው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት በመቃወም አጋርነቱን ለመቀየር ምክንያት እንደሆነም ከጥቂት ወራት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግሯል።

በተጨማሪም ዩክሬን 500 ሺህ ዶላር፣ አዳዲስስ የማንነት እና የጉዞ ሰነዶች እና ለቤተሰቡ ጥበቃ ለማድረግ ቃል እንደገባችለትም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የዩክሬን ባለስልጣናት ፓይለቱ በዩክሬን እንዲኖርም እድል እንደሰጡት ተናግረዋል።

“በእርግጠኝነት እዚህ [ዩክሬን] ቢኖር ጥበቃ ይደረግለት ነበር። በስፔን ውስጥ እንዳደረጉት አሳፋሪ ተግባር እዚህ ያደርጋሉ ብዬ አላምንም” ሲሉም የዩክሬን ብሔራዊ ደኅንነት እና መከላከያ ምክር ቤት ጸሐፊ ኦሌክሲ ዳኒሎቭ ተናግረዋል።

ከሩሲያ ባለስልጣናት ስለ ፓይለቱ ግድያ ምንም አይነት ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም፤ ነገር ግን ማክሰኞ ዕለት የሩሲያ የውጭ የስለላ አገልግሎት ዳይሬክተር ሰርጌይ ናሪሽኪን "ያ ከዳተኛ እና ወንጀለኛ ሞራል የሌለው አስከሬን ነበር" ሲሉም ወርፈውታል።