በሶማሌ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አባላት መካከል የተከሰተው ምንድን ነው?

አቶ ሐቢብ ሐጂ መሐሙድ እና ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ሐቢብ ሐጂ መሐሙድ እና ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ
ታትሟል

የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የቀድሞ አባላት ነን ያሉ አካላት የክልሉን ብልጽግና ፓርቲ 'ለማረም እና ለማስተካከል' በሚል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ ጅግጅጋ ላይ የተሰባሰቡ የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች በቁጥር ከ10 በላይ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞችም ሌሎች የፓርቲው የቀድሞ አባላትና አመራሮች አብረዋቸው መኖራቸውን ገልፀዋል።

ቡድኑ እንቅስቃሴውን 'የክልሉን ሕዝብ ለማዳን' በሚል መጀመሩን ጨምረው ተናግርዋል።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኑኬሽን ኃላፊ የነበሩት እና አሁን የተቃዋሚው ቡድኑ ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ሐቢብ ሐጂ መሐሙድ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት፣ 'የብልጽግና ፓርቲ መስመሩን ስቷል' ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሐቢብ ገለጻ አሁን ያለውን የብልጽግና አመራር በመቃወም የተሰባሰቡት አካላት ከዚህ ቀደም የቢሮ ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላት የነበሩ እና ክልሉን ከ15 እስከ 20 ዓመት በተለያዩ የፖለቲካ ዘርፎች ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው።

የክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ በበኩላቸው እነዚህ ተሰባስበው ተቃውሟቸውን እያሰሙ ያሉ አካላት "ከድርጅቱ አባልነት የተባረሩና ከኃላፊነታቸው የተነሱ ግለሰቦች ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ከኃላፊነታቸው የተባረሩ እና ያኮረፉ ግለሰቦች ስብሰብ ነው" ሲሉ የተናገሩት የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ በፓርቲው ውስጥ ያለውን ስህተት ለማስተካከል እንደ ድርጅት ዝግጅት ላይ ነን ሲሉ አክለዋል።

ኢንጂነር መሐመድ አክለውም በማኅበራዊ ሚዲያዎች የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ተከፋፍሏል በሚል የሚናፈሰው መረጃ "ስህተት እና ተቀባይነት የሌለው" መሆኑን ጨምረው ያስረዳሉ።

አቶ ሐቢብ በበኩላቸው ተቃውሞ እያሰሙ ያሉት የተባረሩ የብልጽግና የቀድሞ አባላት ናቸው የሚለው የጽህፈት ቤት ኃላፊውን ምላሽ "ሐሰት" ሲሉ አጣጥለውታል።

አቶ ሐቢብ አክለውም በፓርቲው ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲሁም በሁሉም ደረጃ ሙስና መኖሩንም ይናገራሉ።

አክለውም የክልሉ መንግሥት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን አስሯል በሚል ተጨማሪ ክስ ያቀርባሉ።

አቶ መሐመድ በበኩላቸው ፓርቲው በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሄድ እና አስፈላጊውን ማስተካከያ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

አቶ መሐመድ ሻሌ የተቃዋሚ አባላት ታስረዋል የሚለውን ክስ ውድቅ አድርገዋል።

በገዢው ፓርቲ ውስጥ አሉ ያሏቸውን ችግሮች አንስተው ተቃውሞ እያሰሙ ያሉት ግለሰቦች በፓርቲው ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን ከማንሳታቸው ባሻገር ሌሎችም ነገሮችን ጠቅሰዋል።

በዚህም በድርቅ የተጎዳው የክልሉ ሕዝብ በቂ ድጋፍ እየተደረገለት አይደለም የሚሉት አቶ ሐቢብ፣ የኑሮ ውድነት በሕዝብ ላይ እያስከተለ ስላለው ጫና፣ በክልሉ ስላለው የወጣቶች ሥራ አጥነት ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል እንደሚገኙበት ይናገራሉ።

በአጠቃላይ ሕዝቡ 'የወደፊት ራዕዩ' የጨለመ አካሄድ በክልሉ ሰፍኗል ሲሉ የሚናገሩት አቶ ሐቢብ፣ በስልጣን ላይ ያሉት የፓርቲው አባላት በቂ ልምድ እና እውቀት የላቸውም ሲሉ ይተቻሉ።

የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ ግን ከፓርቲው እራሳቸውን የነጠሉት ግለሰቦች ያቀረቧቸው ክሶች ተቀባይነት የሌላቸውና ክልሉ ለተጠቀሱትን ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ፓርቲውና የክልሉ መስተዳደር የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።