በርካታ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች በአነስተኛ ዋጋ በበይነ መረብ ላይ ለሽያጭ ቀረቡ

ለገበያ የቀረበ የኢትዮጵያ ቅርስ

የፎቶው ባለመብት, eBay

የምስሉ መግለጫ, ለገበያ ከቀረቡት የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ
ታትሟል

በርካታ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች እንደ ኢቤይ እና አማዞን ባሉ የኢንተርኔት መገበያያ ገጾች ላይ በአነስተኛ ዋጋ ለሽያጭ ቀረቡ።

እነዚህ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ እንደሆኑ የተገመቱ ቅርሶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በብዛት በበይነ መረብ የግብይት መድረኮች ርካሽ በሚባል ዋጋ እየተሸጡ እንደሆነ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ቅርሶች ውስጥ በርከት የሚሉት "ኢቤይ" በተሰኘው የበይነመረብ ገበያ ላይ እንደቀረቡ መመልከት ይቻላል።

ይህ በድንገት በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ገበያ መውጣት ምናልባት በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ የተዘረፉ ናቸው የሚለውን ጥርጣሬ አጭሯል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀውስን ጦርነት ተከትሎ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በክርስትና እና እስልምና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት ስለማድረሳቸው ከዚህ ቀደም ተዘግቧል።

በሃይማኖት ተቋማት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ጥንታዊ ቅርሶች ስለመዘረፋቸው ተገልጿል።

በጉዳዩ ላይ የፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ምላሽና ማብራሪያን ለማግኘት ቢቢሲ በተደጋጋሚ ያደረገው የስልክ ጥሪ ባለመነሳቱ ለጊዜው ሳይሳካ ቀርቷል።

የቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም በጉዳዩ ዙርያ ያነጋገራቸው የቋንቋ ታሪክ ተመራማሪ እና በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ዶክትሬት ተማሪ የሆኑት ሐጎስ አብረሃ (ዶ/ር) በጦርነቱ ወቅት "ከበርካታ የትግራይ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናትን ቅርሶች መዘረፋቸውን አረጋግጫለሁ" ይላሉ።

ሐጎስ (ዶ/ር) በወቅቱ ከተዘረፉት ቅርሶች አንዳንዶቹ ጥንታዊና እጅግ ብርቅዬ የነበሩ ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ተመራማሪው ከኢትዮጵያ የተዘረፉት ቅርሶች በብዛት እየተሸጡ ያሉበት ዋጋ እጅግ ርካሽ የሚባል እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጠዋል።

በዚህ ወቅት እንዴት ተዘርፈው ከአገር ሊወጡ እንደቻሉ ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በሱዳንና ኬንያ በኩል ሊሆን እንደሚችል ግን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

በኢቤይ የበየነመረብ የግብይት መድረክ ላይ ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ ከኢትዮጵያ የሆኑ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ለሽያጭ ካቀረቡት ሻጮች መካከል አንዱ ዎርሌይ ኢንተርፕራይስ ኢንተርናሽናል ኤልኤልሲ (Worley Enterprises International LLC) የተሰኘው ሻጭ ይገኝበታል።

ይህ ነጋዴ ለሽያጭ ካቀረባቸው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርጾች መካከል አንዱ ከ15ኛው አስከ 17ኛ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ በእጅ የተጻፈ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ይገኝበታል።

ይህ በእንስሳት ቆዳ ላይ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፈ ጽሑፍ ጥር 12/2014 ዓ.ም. በ240 የአሜሪካ ዶላር ለገበያ ቀርቧል።

ሌላኛው ከ15ኛው አስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ባሉት ዓመታት በግዕዝ ቋንቋ ሳይጻፍ አይቀርም የተባለለት መጽሐፍ በ1250 የአሜሪካ ዶላር በዚሁ ገጽ አማካይነት ለገበያ ቀርቧል።

እንደ ኢቤይ ባሉ የኢንተርኔት ገበያዎች ላይ ግለሰቦች ምዝገባ አድርገው መግለጫ እና ፎቶ በማያያዝ እቃዎችን ለገበያ ያቀርባሉ።

ዎርሌይ ኢንተርፕራይስ ኢንተርናሽናል ኤልኤልሲ ያስተዋወቃቸው መነሻቸው ከኢትዮጵያ የሆኑ ቅርሶች "መቶ በመቶ ትክክለኛ" ስለመሆናቸው በመግለጽ፤ ገዢዎች "ይህ መልካም እድል እንዳያመልጣችሁ" በማለት ሰዎች ቅርሶቹን እንዲገዙ ያበረታታል።

ይህ ሻጭ ለሽያጭ በሚያቀርባቸው እቃዎች መግለጫ ላይ፤ መሰል ጥንታዊ እቃዎችን ለሽያጭ የሚያቀርበው ሰዎች እቃዎቹን እንዲሸጡለት ከሰጡት በኋላ እንደሆነ ይገልጻል።

ከዚህ በተጨማሪም እራሱ በተለያዩ ወቅቶች ከሰበሰባቸው ክምችቶቹ አልያም ከሌሎች ስፍራዎች ገዝቶ ኢቤይ ላይ መልሶ ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ያትታል።

ለ15 ወራት ያክል የዘለቀው የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት በእምነት ስፍራዎች ላይ ካደረሰው ጉዳት ባሻገር፣ ከባድ የሚባል ውድመትን እንዲሁም ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል።

በጦርነቱ ሳቢያ ቁጥራቸው አስካሁን በውል ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለከፋ ረሀብ ያጋለጠ ሲሆን፣ ወደ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ሰብዓዊ እርዳታን እንዲጠብቁ መገደዳቸውን ድርጅቱ አመልክቷል።