እየሩሳሌም የተወለዱ አሜሪካውያን ፓስፖርት ላይ እስራኤል የትውልድ አገር ልትባል ነው

ታትሟል

እየሩሳሌም ውስጥ የተወለዱ አሜሪካውያን ፓስፖርታቸው ላይ እስራኤል የትውልድ አገር ተብላ እንድትመዘገብ ውሳኔ ተላለፈ።

የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ቀድሞ የነበረውን ፖሊሲ ቀይሮ ነው ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው።

ከዚህ ቀደም እየሩሳሌም የተወለዱ አሜሪካውያን ፓስፖርት ላይ እስራኤል እንደ አገር አትጠቀስም ነበር።

እስራኤል፤ እየሩሳሌም ዋና ከተማዬ ናት እንደምትል ይታወቃል። ፍልስጤማውያን በወረራ የተያዘው ምሥራቃዊ ክፍል አገር ሲመሠርቱ መዲናቸው እንደሚሆን ይናገራሉ።

ትራምፕ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2017 ላይ እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ናት ብለው እውቅና መስጠታቸው ይታወቃል። የአሁኑ ውሳኔም ይህንን አቋማቸውን ያጠናክራል።

ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ማለታቸው የአረብ አገራትን አስቆጥቷል። ለዓመታት አሜሪካ ስታራምደው ከነበረው ፖሊሲ ጋርም ይቃረናል።

እስራኤል ምሥራቅ እየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው በ1967 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሲካሄድ ነው። ከዛም አካባቢውን የግዛቷ አካል አድርጋዋለች።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዚህ የእስራኤል ድርጊት እውቅና አይሰጥም።

የእየሩሳሌም ጉዳይ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል መቃቃር ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ ሲሆን፤ ሁለቱም ወገኖች ችግሩን በድርድር ለመፍታት ጥረት አድርገው ነበር። ለ25 ዓመታት የዘለቀው የሰላም ድርድር ግን አንዳችም ደረጃ አልደረሰም።

እየሩሳሌም ውስጥ የተወለዱ አሜሪካውያን ፓስፖርት ጉዳይ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው በ2015 ነበር። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን መለወጥ የሚችለው የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ብቻ እንደሆነ ውሳኔ አሳልፎም ነበር።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ የአሜሪካን አቋም በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል።

ትራምፕና የዴሞክራት እጩው ጆ ባይደን የሚፋለሙበት የአሜሪካ ምርጫ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት የተላለፈ ውሳኔ ነው።

2018 ላይ አሜሪካ የእስራኤል ኤምባሲዋን ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም ማዘዋሯን ጆ ባይደን መቃወማቸው ይታወሳል።

ፍልስጤማውያን ትራምፕ ለእስራኤል ያደላ እርምጃ ወስደዋል ሲሉ ኮንነዋል። ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነትም አቁመዋል።

ጥር ላይ ትራምፕ ለእስራኤል እና ለፍልስጤም ያዘጋጁት የሰላም ፍኖተ ካርታ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደግፈውን የሁለት አገራት መፍትሔ የተከተለ አይደለም።

የሁለት አገራት መፍትሔ ፍልስጤም ራሷን የቻለች አገር እንደሆነች እውቅና ይሰጣል።

ባይደን የዚህ የመፍትሔ ሐሳብ ደጋፊ ናቸው።

በያዝነው ሳምንት በ18 አገሮች የተሠራ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፤ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ዜጎች ባይደንም ይሁን ትራምፕ ለቀጠናው ይበጃሉ ብለው አያምኑም።

ሆኖም ግን አብዛኞቹ ዜጎች ባይደን ፕሬዘዳንት እንዲሆኑ ይፈልጋሉ።