ትራምፕ የጎላን ተራሮች የእስራኤል ግዛት ናቸው ብለው እውቅና ሊሰጡ ነው

ታትሟል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል እ.አ.አ. በ1967 ከሦርያ የወሰደችውን የጎለን ተራሮችን ግዛት የእስራኤል ነው ብሎ በመቀበል ለዓመታት ተይዞ የነበረውን የአሜሪካን ፖሊሲ ቀይረዋል። በትዊተር ገፃቸው ትራምፕ ቦታው "ለእስራኤልና በዙሪያው ላሉ ሃገራት ደህንነት ወሳኝ ቦታ ነው" ብለዋል።

እ.አ.አ በ1981 እስራኤል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባልተቀበለው መንገድ ጎላንን ተቆጣጥራለች።

ቦታውን ዳግመኛ ለመውሰድ የምትፈልገው ሦሪያ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ምንም አስተያየት አልሰጠችም። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በትዊተር ገፃቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕን አመስግነዋል።

"ኢራን ሦሪያን ተጠቅማ እስራኤልን ለማጥፋት እየሞከረች ባለችበት ጊዜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የእስራኤልን በጎላን ተራሮች ላይ ያላትን ሉዓላዊ ሥልጣን ተቀብለዋል" ብለዋል ቤንጃሚን ኔታንያሁ።

ሪቻርድ ሃስ የተባሉት የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት የፕሬዚዳንት ትራምፕን ውሳኔ አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልፀዋል። ትራምፕ እስራኤል በጎላን ግዛት ላይ ያላትን ሥልጣን መቀበል የተባበሩት መንግሥታትን "ማንም በጦርነት መሬት መቀበል አይችልም" የሚለውን ሕግ የጣሰ ነው ብለዋል።

ሪቻርድ ሃስ ይህን የተናገሩት ቤንጃሚን ኔታንያሁ በቅርብ የሚጠብቃቸው ምርጫ ላይ እያሉ ሲሆን ብዙ የሙስና ክሶችም ተመሥረተውባቸው ሳለ ነው።

እ.አ.አ በ2017 ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆንዋን ተቀብለው የአሜሪካን ኤምባሲ ከቴላቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንዲዘዋወር አዘው ነበር። ውሳኔያቸውም በፍልስጤማውያን ውግዘት የደረሰበት ሲሆን የተባበሩት ምንግሥታትም ውሳኔው ውድቅ እንዲሆን ጠይቆ ነበር።

ለኔታንያሁ መልካም ያልተጠበቀ ዜና

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዊት ለቅርብ ባልደረቦቻቸው እራሱ ያልተጠበቀ ውሳኔ ይሆን?

ውሳኔው ያልተጠበቀ ከሆነ በእርግጥም ለኔታንያሁ መልካም ዜና ነበር። "በጣም ደሽተኛ ነኝ" ነበር የመጀመሪያ ንግግሩ።

ያልተጠበቀ ያደረገው ግን የተነገረበት ጊዜ እንጂ ውሳኔው እንኳን በትራምፕ አስተዳደር ሲታሰብበት የቆየ ነገር ነው።

የአሜሪካ በይፋ ጎላንን የእስራኤል ግዛት አድርጋ መቀበል በተግባር ምንም ነገር አይቀይርም፤ ምክንያቱም እስራኤል ሙሉ ወታደራዊ ኃይሏን በማስፈሯ ነው።

ስለዚህ ገምጋሚዎች ውሳኔው ኔታንያሁን በቅርብ በሚካሄደው የተሟሟቀ ምርጫ ላይ ድምፃቸውን ለመጨመር የተደረገ ሙከራ ነው ብለዋል።

እንደዚህ ከሆነ የዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ ውሳኔ ነው ብለዋል። "ትራምፕ የተነጠቀን ግዛት እውቅና ከሰጠ ሩስያ ዩክሬን ላይ ያደረገቸውን ተመሳሳይ ድርጊት የመኮነን መብት የለውም"።

ተራሮች ስፍራ የት ነው?

ቦታው ከሦሪያ ዋና ከተማ ከደማስቆ በደቡብ ምዕራብ 60 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን 1 200 ካሬ ስፋት አለው።

እስራኤል ብዙውን ሽፋን ከሦርያ የነጠቀችው እ.አ.አ. በ1967 ወደ መጨረሻዎቹ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ነው። እ.አ.አ በ1973 የሦርያን ግዛት መልሳ የመውሰድ ሙከራ በእስራኤል አሸናፊነት ከሽፏል።

ሁለቱ ሃገራት በመጪው ዓመት ወደ 70 ኪሜ የሚሆን ከወታደር ነፃ የሆነ በተባበሩት መንግሥታት ቁጥጥር ስር የሆነ ክልል ለመፍጠር የተስማሙ ቢሆንም ሃገሮቹ በጦርነት ቀጥለዋል።

ሦርያ፤ እስራኤል ሙሉ የጎላን ስፍራ ለቅቃ ካልወጣች የሰላም ስምምነት አልፈርምም ስትል፤ የመጨረሻው በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የተደረገው ስምምነትም እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም ፈርሷል። ቱርክ እ.አ.አ በ2008 ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሁለቱን ሃገራት ለማስማማት ሞክራለች።

በጎላን ውስጥ ከ30 በላይ የእስራኤል ሰፈራዎች ሲኖሩ ለ20 000 የሚጠጉ ሰዎችም መኖሪያ ናቸው። እስራኤል ብትቃወምም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የመኖሪያ ስፍራዎቹ ሕገወጥ ናቸው።

ጎላንን በእስራኤል ስትያዝ ለቅቀው ያልወጡት 20 000 ሦሪያውያን ከሰፋሪዎቹ ጋር አብረው ይኖራሉ።