ስድስት የዩኬ ወታደሮች በአደንዛዥ እፅ ዝውውር ተጠርጥረው ታሰሩ

ታትሟል

በዩናይትድ ኪንግደም ስድስት ወታደሮች እንዲሁም አንድ የወታደር መኮንን በአደንዛዥ እፅ ዝውውር እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመል በሚሉ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ስድስቱ ወታደሮች አይሪሽ ጋርድስ በሚባለው ምድብ ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን፣ አንደኛው መኮንን ደግሞ ኮልድስትሪም ጋርድስማን የተባለው ምድብ ውስጥ ዘለግ ላለ ጊዜ ያገለገሉ ናቸው።

የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮቹ የታሰሩት ቀደም ብሎ በተጀመረ ኦፕሬሽን ነው ብሏል።

አይሪሽ ጋርድስ የተባለው ምድብ የፊታችን ሰኔ በሚካሄደው የንግሥቲቷ የ70 ዓመት ኢዮቤልዮ ላይ ትዕይንት እንዲያሳይ ይጠበቃል።

ሆኖም ግን በቁጥጥር ስር የዋሉት ስድስት አባላቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደማይገኙ ተገልጿል።

አይሪሽ ጋርድስ የተመሠረተው እአአ በ1900 ሲሆን፣ ዩኬ ወደ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ካሰማራቻቸው ወታደሮች መካከል ይገኙበታል።

ይህ ምድብ ተጠሪነቱ ለልዑል ዊልያም ሲሆን፣ ረዣዥም ቀይ ኮፍያ የሚያደርጉ አባላቱ ቤተ መንግሥትም ይጠብቃሉ።

የመከላከያ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ እንደተጠቀሰው፣ ወታደሮቹን ለመያዝ ኦፕሬሽን ከተጀመረ ቆየት ብሏል።

አደንዛዥ እፅ ለማዘዋወር በመመሳጠር እንዲሁም ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ተጠርጥረውም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

"መከላከያው ማንኛውንም ሕገ ወጥ ድርጊት አይታገስም" ብሏል መከላከያ ሚኒስትር በመግለጫው።